በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዚምባብዌ - ያች ቀን እነሆ ደረሰች


የዚምባብዌ መሪ ሮበርት ሙጋቤ
የዚምባብዌ መሪ ሮበርት ሙጋቤ

የዚምባብዌው የረዥም ጊዜ መሪ ሮበርት ሙጋቤ ዋና ከተማዪቱ ሃራሬ ውስጥ “በቁም እሥር” ላይ መሆናቸውን የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ጄከብ ዙማ አረጋግጠዋል። ሮበርት ሙጋቤ ከ37 ዓመታት የፕሬዚዳንትነት ዘመን በኋላ ወታደራዊ ድጋፍ ባለው እንቅስቃሴ ዛሬ ከመንበረ ሥልጣናቸው ተገፍተው ወጥተዋል።

የሮበርት ሙጋቤ የአርባ ዓመት ሥርዓተ-መንግሥት ያከተመ ይመስላል። በአንድ ወቅት ታማኛቸው የነበሩት የጦር ጄነራል የመንግሥቱን የቴሌቪዥን ጣቢያ ተቆጥረው የዘጠና ሦስት ዓመቱን አዛውንት ፕሬዚዳንትና ባለቤታቸውን በጥበቃ ሥር አውለዋቸዋል። የጦር ሠራዊቱም ፓርላማውን ከብቧል።

ሮበርት ሙጋቤ እኮ አብዮተኛ፣ የነፃነት ተዋጊ፣ ጀግናና አርበኛ ሆነው ተወድሰዋል - በዕድሜ ዘመናቸው።

በ1917 ዓ.ም. (በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር) ያኔ ሮዴዥያ ትባል በነበረች ግዛት ውስጥ የተወለዱት ሮበርት ጋብሪየል ሙጋቤ በ1967 ዓ.ም. ከፍ ወዳለው የፖለቲካ አመራር ዘለቁ። ያኔ ታዲያ ምሁሩ እና የቀድሞ አስተማሪ ሮበርት፣ ሮዴዥያን ቀፍድዶ ከያዛት የነጭ የበላይነት አገዛዝ ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቀው ዱር የወጡት የተራዘመው የሽምቅ የነፃነት ተዋጊ አርበኛ ሮበርት ገና ከእሥራት መፈታታቸው ነበር። በሁከተኛነት ተፈርዶባቸው ለአሥር ዓመታት ዘብጥያ ነበሩ።

“የሕዝብ መሪ ለመሆን አቋራጭ መንገድ የለም፤ ነፃነታችንን ለመቀዳጀት አቋራጭ እንዳልነበረ ሁሉ፤ ረዥሙን መንገድ መጓዝ ይገባናል” ብለው ነበር ሙጋቤ ያኔ

1973 ዓ.ም. – አዲሲቱ ዚምባብዌ ተወለደች። (በዚህ ዘገባ ውስጥ ተለይቶ እስካልተነገረ ድረስ ጊዜ የሚጠራው በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ነው) ሮበርት ሙጋቤም የወጣቱ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኑ። በነዚያ የመራኄ መንግሥትነት ሥልጣን ዘመናቸው የመጀመሪያ ዓመታት ታዲያ ሙጋቤ በሣል፣ ቆራጥና ተጨባጭ በተባለ የአስተዳደር አያያዛቸው እጅግ የተሞገሡ፣ ብዙ የተዘመረላቸውና የተጨበጨበላቸውም ሆኑ። እናም ወራት በወራት፣ ዓመታት በዓመታት ላይ እየተደራረቡ በመጡ መጠን በቀጣዮቹ አሥሮች ዓመታት ውስጥ እንያ ብልህ መሪ የሥልጣናቸውን መደላድል እያጠናከሩ ቀጠሉ። በተቃዋሚዎቻቸው ላይም በጭካኔ የታጀበ ብተና ማሳደድና ሁከትን አበረቱ። በሺሆች የሚቆጠሩ ዚምቧቤያዊያንም ሕይወት በዚያ ውስጥ ረገፉ።

የዓለም 0ይኖች ዛሬ ሃራሬ ላይ ናቸው። የዛዪቱ ዕለት ሃራሬ ላይ እንደምትመጣ ማንም አያውቅም ነበር፤ ይህች ቀን እንደምትመጣ ግን ሁሉም ሰው ያውቅ ነበር። ጋዜጠኞች ሲናገሩ አንደበታቸው እንዲዘጋ ተደርጓል። በቅርብ ዓመታት ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዚምባቤያዊያን ወደ ጎረቤት ደቡብ አፍሪካ እየተሰደዱ ከለላና ጥገኝነት ሊሹ ወጥተዋል።

ዛሬ፣ በዛሬዪቱ ዕለት የዚምባብዌ ዕጣ ምን ሊሆን እንደሚችል ለመገመት በሚያስቸግር የመጨረሻ መጀመሪያና፣ የመጀመሪያዎች መጀመሪያ ላይ ትገኛለች።

በዕድሜም በእጅጉ የበለጠጉት ፕሬዚዳንት ምክትላቸውን ኤመርሰን ምናንጋግዋን ባለፈው ጥቅምት 25 ያባረሩ ጊዜ፣ ፍቅር በራቃቸው ባለቤታቸው በግሬስ ሙጋቤም ወንበሩን ለመሙላት ባሰቡ ጊዜ የሠራዊቱ አለቃ ከፋቸው፤ ተቆጡ፤ መሪው የተባራሪውን ምክትል ፕሬዚዳንት ደጋፊዎች ማዋከብና ማባረርን ካላቆሙ ሠራዊቴን ይዤ ሃራሬ እገባለሁ አሉ - ትናንት፤ ማክሰኞ፤ ኅዳር 5፣ .....

ይህ ሁኔታ አሉ፤ የዓለምአቀፉ ግጭትና ቀውስ አነፍናፊና መፍትኄ አፈላላጊ ቡድን አይሲጂ ተንታኝ ፒዬር ፒጉ። “ባለፈው ሣምንት ውስጥ፣ ባለፉ ጥቂት ቀናት ሁኔታው አብዝቶ እየተበላሸ ሲመጣ አንዳች ነገር እንደሚወለድ’ኮ ግልፅ ነበር። ጣልቃ እገባለሁ ያሉ ጊዜ ብዙው ሰው እንዲያው ልፍለፋ ብጤ ነገር መስሎት ነበር። አይገቡም፣ ሙጋቤም ሥልጣናቸውን የሙጥኝ እንዳሉ ይዘልቋታል እንጂ ፍንክች አይሉም፤ ምንም ቢመጣ ያከሽፉታል ያሉ ብዙ ነበሩ” ብለዋል ፒጉ።

ለካስ የዚምባብዌ ጦር ዋና አዛዥ ጄነራል ኮንስታንቲን ቺዌንግዋ ልፍለፋ አልነበረም ያደረጉት። ረቡዕ፣ ኅዳር 6 /2010 ዓ.ም. (ዛሬ)፤ ወታደሩ ያሉትን ፈፀሙ። ትናንት ሃራሬ ውስጥ ያጓሩ የነበሩ ታንኮች ዛሬ ነጋ አልነጋ ብለው ማለዳው ላይ በመንግሥት እጅ የሚገኘውን የሃገሪቱን ቴሌቪዥን ጣቢያ ተቆጣጠሩና የጦሩ ቃል አቀባይ የሆኑት ሜጄር ጄነራል ሲቡሲሶ ሞዮ ዚምባብዌን ክው ያደረገ፣ የዓለምን ጆሮዎች ድንገት ያቀና መግለጫ ሰጡ።

“ጓድ አር ጂ ሙጋቤና ቤተሰባቸው በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፤ ደኅንነታቸው የተጠበቀ ነው። እኛ እያነጠጠርን ያለነው እርሣቸውን ከብበዋቸው የኖሩ ወንጀሎችን ሲፈፅሙ የነበሩ፣ በሃገሪቱ ውስጥ ማኀበራዊና የምጣኔ ኃብት ጉስቁልና እንዲበዛ ያደረጉ ወንጀለኞችን ፍትሕ ፊት ለማቅረብ ነው”

ገዥው ዛኑ-ፒኤፍ ከአሥር ቀናት በፊት በሙጋቤ የተባረሩት ምናንጋግዋን እመልሳለሁ፤ ብሏል። ሕገ መንግሥቱም እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል።

እነሆ ዚምባብዌ በሚባል መድረክ ላይ ድራማው ተጀምሯል - እያሉ ነው የግራና የቀኝ ተንታኞች።

ሮበርት ሙጋቤ መሬትን ከነጭ ገበሬዎች ነጥቀው መሬት ለሌላቸው ጥቁሮች ለመሸንሸን የወሰዱት እርምጃ ዚምባብዌን ከዳቦ ቅርጫትነት ወደ ባዶ ቅርጫትነት ለውጧታል እያሉ የሚነቅፉ ብዙ ናቸው።

የዚምባብዌ የገንዘብ ግሽበት በመቶና በሼህ መቶኛዎች ያናጠረ ሆነ። የዚምባብዌ ዶላር ወደቀ፣ ዋጋ አጣ፣ ከምንዛሪው ገበያ ወጣ። ሥራ አጥነት ሃገሪቱን ዋጣት።

የዛሬ ዘጠኝ ዓመት አካባቢ ዚምባብዌ ባካሄደችው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የመጀመሪያው ዙር የተቃውሞው መሪ ሞርጋን ቻንጊራይ ሙጋቤን የማሸነፋቸው ዜና ፓርቲያቸውን ዛኑ-ፒኤፍን እራሳቸውን ፕሬዚዳንቱንም በእጅጉ አስደነገጠና በተቃዋማዎቻቸው ላይ የበረታ ሽብርና ሁከት እንዲነዙ አነሳሳቸው። ይህ ማሳደድ ቻንጊራይ ያኔ እራሣቸውን ለማግለልና በሁለተኛው ዙር ላለመወዳደር ወደመገደድ ወሰዳቸው። እነሆም ሥልጣን ለሙጋቤ ፀናች።

ከአራት ዓመታት በኋላም በ2005 ዓ.ም. ዚምባብዌ ባካሄደችው ምርጫ ሙጋቤ እንደገና አሸነፉ ተባለ። በዚያን ጊዜ’ኮ ታዲያ ዚምባብዌ ድሮ የመከራ ምድር፣ የዓለም ጭንቀት ሆና ነበር። ‘ሙጋቤም ከተለመዱት የአፍሪካ አምባገነኖች አንዱ ናቸው’ ሲል ዓለም መስክሮና ደምድሞ ተቀምጧል። አምባገነን! አገዛዙ በሙስና፣ በምጣኔ ሃብት ዝርክርክነትና ብክነት የተጨማለቀ፤ ለተቃውሞ ትዕግሥት፣ ልቦናና ብልኅነት ጨርሶ የጠፉበት … አምባገነን።

ዓለም የሚሰማውን መናገር ጀምሯል።

የአሪዞናው ሪፐብሊካን የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ጄፍ ፍሌክ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል - “የነገሮች አካሄድ መፈንቅለ መንግሥት ይመስላል” ብለዋል። ሮበርት ሙጋቤንም “እጅግ ረዥም ዓመታት ያገለገለ ወንበዴ” ብለው ጠርተዋቸዋል።

ለተጨማሪና ለፖለቲካ ሣይንስ ፕሮፌሰሩ ዶ/ር ጌታቸው መታፈሪያ ትንታኔ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

ዚምባብዌ - ያች ቀን እነሆ ደረሰች
please wait

No media source currently available

0:00 0:12:57 0:00

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG