የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች፣ ካለፈው ወር ሚያዝያ ሰባት ቀን ጀምሮ፣ በካርቱም እና በሌሎች አካባቢዎች በሚያካሒዱት ግጭት ምክንያት፣ 25ነጥብ7 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች፣ አስቸኳይ ሰብአዊ ርዳታ ፈላጊዎች ኾነዋል።
ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት(IOM)፣ ረቡዕ ዕለት ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፣ በመላው ሱዳን ቢያንስ 843ሺሕ130 ሰዎች ሲፈናቀሉ፣ ወደ 259ሺሕ የሚደርሱ ሰዎች ደግሞ ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል።
ግጭቱ ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ፣ ኢትዮጵያንና ሱዳንን ወደምታገናኘው መተማ ከተማ፣ በቀን ከ700 እስከ 800 የሚደርሱ ሰዎች፣ የሱዳንን ድንበር ተሻግረው ይገባሉ። የቻይና ማዕከላዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ የኾነው ሲሲቲቪ ከአነጋገራቸው ስደተኞች መካከል አንዱ የኾነው እስማኤል ሁሴን፣ ግጭቱ ከመጀመሩ በፊት፣ እሱ እና ነፍሰ ጡር ሚስቱ፣ በካርቱም ይኖሩ እንደነበር ገልጾ፣ አለመረጋጋቱ መኖሪያ ቤታቸውን ጥለው እንዲሰደዱ እንዳስገደዳቸው ይናገራል።
“እዚኽ ለመድረስ በጣም ብዙ ቀናትን ወስዶብናል። በየመንገዱ የፍተሻ ጣቢያዎች አሉ። ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ከደረስን በኋላ፣ ለሌላ ዙር የደኅንነት ፍተሻ ወደ አልቃድሪፍ ተልከን ነበር፤” የሚለው እስማኤል፣ መተማ ለመድረስ፣ ለእርሱ እና ለነፍሰ ጡር ባለቤቱ በጣም ከባድ እንደነበርና በሱዳን የነበረውን ሁሉንም ነገር በማጣቱ ሕይወትን እንደገና ከምንም መጀመር እንዳለበት ገልጿል።
በሱዳን ይሠሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያንም፣ ደኅንነታቸውን ለማረጋገጥ ሌላ አማራጭ ስላልነበራቸው ወደ ትውልድ ሀገራቸው ተመልሰዋል። ከእነዚኽ አንዱ፣ በሱዳን ስደት ላይ ይኖር የነበረው ነብሱ መሐመድ ኑር አንዱ ነው።
በዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት(IOM) የኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቢባቱ ዌን-ፎል እንደሚያስረዱት፣ ከሱዳን እየሸሹ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ስደተኞች፣ አስቸኳይ መሠረታዊ ርዳታ የሚያስፈልጋቸው ቢኾንም፣ በቂ ድጋፍ ግን እያገኙ አይደለም።
“ተፈላጊው የርዳታ መጠን እጅግ ከፍተኛ ነው። ከረጅም ጉዞ በኋላ እዚኽ መድረስ የቻሉ ሰዎች አሉ። በአስከፊ ኹኔታ ውስጥ ያሉ፣ የመጠለያ፣ የምግብ፣ የትራንስፖርት፣ የውኃ አቅርቦት እና የመጸዳጃ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ገና እየመጡ ነው። እነዚኽ አገልግሎቶች የሚያስፈልጓቸው ቢኾንም፣ ርዳታው የለም፤” ብለዋል ዌን-ፎል፡፡
የ21 ዓመቷ ሰራዌይን እድሪስ አሌ፣ ገና መተማ ከተማ መድረሷ ነው። ቤተሰቦቿን፣ ጓደኞቿን፣ ጎረቤቶቿንና መኖሪያዋን አጥታለች። “ሰላምንና ደኅንነትን እመኛለኹ። የተኩስ ድምፅ መስማት አልፈልግም፤” የምትለው እድሪስ፣ “የሚሰማኝን ፍርሃት መርሳት ብችልና ትምህርቴን ብቀጥል ደስ ይለኛል። ጤና እና ምግብ እሻለኹ፤ መኖር እፈልጋለኹ፤” ያለች ሲኾን፣ አሁን ለመለወጥ ግን፣ ምኞቷ ብቻ እንደቀራት ትናገራለች።
የሱዳን ጦር፣ በትላንትናው ዕለት፣ በዋና ከተማዪቱ ካርቱም የአየር ድብደባ ማድረጉን ነዋሪዎች ለሮይተርስ ገልጸዋል። ጦሩ ጥቃቱን የፈጸመው፣ አንድ ሳምንት የሚቆየው የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ ከመኾኑ ከሰዓታት በፊት ነው።
በዓለም ጤና ድርጅት መረጃ መሠረት፣ እስከ አሁን በግጭቱ፣ 705 ሰዎች ሲሞቱ፣ ቢያንስ 5ሺሕ287 ጉዳት ደርሶባቸዋል።