በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢትዮጵያ መንግስት የሚዋከቡና የሚታሰሩ ተጠቂዎች ቢመስሉም አሸናፊዎች ናቸው ሲሉ ብርቱካን ሚደቅሳ ተናገሩ


ብርቱካን ሚደቅሳ በእስር ሳሉ እንዲለቀቁ በአሜሪካ የተካሄደ ሰልፍ
ብርቱካን ሚደቅሳ በእስር ሳሉ እንዲለቀቁ በአሜሪካ የተካሄደ ሰልፍ

በታህሳስ ወር በህመም የሞቱት የቀድሞው የቼኮዝላቫኪያ ፕሬዝደንት ቫትስላብ ሃቨል፤ ቼኮስላቫኪያን ከኮሚውኒስት አገዛዝ ነጻ ለማውጣት “የቬልቬት አብዮት” በመባል በሚታወቀው ሰላማዊ ትግል በ1981ዓም የቼኮዝላቫኪያ ፕሬዝደንት ሆኑ። በ1985 ቼኮዝላቫኪያ ለሁለት ተከፍላ ስሎቫኪያና ቼክ ሪፐብሊክ ስትባል፤ የመጀመሪያው የቼክ ፕሬዝደንት ሆነው አገልግለዋል።

ቫትስላቭ ሃቨል በመላው አለም የሚታወቁት በፖለቲካቸው ብቻ አይደለም። እንዲያውም ሃቨል ከምንም በላይ እራሳቸውን የሚገልጹት፤ ጸሃፊ ተውኔት አድርገው ነው። የሃቨል ተውኔቶች ታዲያ፤ ፍሬ ከርስኪ አልነበሩም፤ መሰረታቸው እውነት ሆኖ የቼኮችን ህዝና የዓለምን ህዝብ አንድ የሚያደርጉ ሰብዓዊ ባህርያትና ፍላጎቶች ጣራና ድግድዳ ሆነው የተዋሃዱባቸው ናቸው። የተውኔቶቹ ክዳን ደሞ፤ ነጻነት፣ ተስፋና ዴሞክራሲ ነበሩ።

ቼኮዝላቫኪያ የተፈጠረችው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ ሲሆን፡ አስቀድማ በጀርመኖች ጠንካራ እጅ ትገዛ የነበረችው የምስራቅ አውሮፓ አገር፤ ቀጥላ በራሻ ኮሚኒስቶች እጅ ወደቀች።

በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ቼኮዝላቫኪያ የምእራባዊያንና የምስራቅ ሶሻሊስቶች የመቆራቆሻ ሜዳ ነበረች።

በዚህ የቁርሾ ጊዜ የኖሩት ሃቨል፤ ስራዎቻቸው የጊዜውን ሁኔታዎች ያሳዩ ነበር። ይሄ ታዲያ በሶሻሊስቶቹ አልተወደደላቸውም። በተለይ ስለ ግለሰቦች ነጻነት፣ እኩልነትና ዜጎች እራሳቸውን ለማስተዳደር ያላቸውን መብቶች የሚያሳዩ መልእክቶች ለተደጋጋሚ እስራትና ወከባ ዳርጓቸዋል።

በ1980ዎቹ ሃቨልና መሰል ዜጎቻቸው በሰላማዊ መንገድ የሶሻሊዝም አስተዳድርን ለመጣል ተደራጅተው ተንቀሳቀሱ። መሳሪያቸው ንግግር፣ ብእርና ጠብቆ የህዝቡን ብሶት የማደራጀት ብቃት ነበር። ተሳካላቸው። አንድም ሰው ሳይሞት “በቬልቬት አብዮት” የሰላማዊ ትግል ሶሻሊስቶችን አሽቀንጥረው ጣሉ።

በዚያን ወቅት በቼኮዝላቫኪያ የዩናይትድ ስቴይትስ አምባሳደር ዊሊያም ሉርስ፤ ሃቨል ፕሬዝደንት ከመሆናቸው አንድ ቀን አስቀድሞ አብረዋቸው እራት በልተው ነበር።

“የቆዳ ጃኬት ለብሰው በየመንገዱ ሰልፍ ያስተባብሩ የነበሩ የፋብሪካ ሰራተኞች፤ በአዲሲቱ ቼኮዝላቫኪያ የካቢኒ ሚኒስትሮች ሆኑ” ብለዋል።

ለዴሞክራሲ በሚሰራው National Endowment for Democracy ባሰናዳው የሃቨል መታሰቢያ ፕሬዝደንት ኦባማ በአካል ባይገኙም በቢል ክሊንተን አስተዳድር ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር የነበሩት ማድሊን ኦልብራይት መልእክታቸውን እንዲያነቡ ጠይቀዋቸዋል።

“ሁላችሁም ጋር በአንድነት የቫትላቭ ሃቨልን ህይወትና ስራዎች ስዘክር ደስታ ይሰማኛል። ከጸሃፊ ተውኔትነት፣ ወደ ፖለቲካ እስረኛነት፣ ከዚያ ወደፕሬዝደንትነት ያደረጉትጉዞ፤ ነጻነትን ለሚሹ የአለም ህዝቦች አርዓያ ሆኗል።”

በዋሽንግተን ዲሲ ሃቨልን ለማስታወስ በተሰናዳው ዝግጅት በርካታ የአለም ታዋቂ የፖለቲካ መሪዎችና መልእክተኞች ተገኝተዋል። ከኩባ፣ እስከ ሞንጎሊያ፣ ቲቤት፣ በርማ፣ ኢትዮጵያ፣ አሜሪካና ቼክ የታወቁ ስሞች ይህንን የነጻነት ሰው ዘክረዋል።

የቲቤት ህዝቦች የመንፈሳዊ መሪ ዳሊ ላማ በጽሁፍ መልእክታቸውን ልከዋል።

“ከቲቤታዊያን ጎን ተሰልፈዋል። በጋራ ያረቀቁት የሰብዓዊ መብት ቻርተር 77 በአገራቸው ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ዜጎችም ትልቅ ለውጥ ያመጣ ነው። በቅርቡ ቻርተር 8 የሚባል ተመሳሳይ ህግ በቻይና ረቋል። በቃላት ብቻ ሳይሆን ጓደኝነታቸውን በተግባር አሳይተዋል። የቻይና ተቃዋሚ ሉ ሻቦ ከእስር እንዲፈታም ተከላክለዋል” ይላል የዳሊ ላማ መልእክት።

ቫትስላቭ ሃቨል የጤንነት ሁኔታቸው እያስቆለቆለ ባለበት ወቅት በጋዜጠኞች ተከበው ፕራግ ለሚገኘው የቻይና ኢምባሲ ሉ ሻቦን መንግስቱ እንዲለቅ ደብዳቤ አስገብተዋል።

ሃቨል ጤንነታቸው እያሽቆለቆለ በመጣበት ጊዜም የሌሎችን ህዝቦች ትግል አልረሱም። በበርማ ከወታደራዊ አገዛዝ ጋር ተፋጠው በእስርና በወከባ የሚጎሳቆሉት አን ሳን ሱቺ ሃቨል ካረፉ ከሁለት ቀናት በኋላ ደብዳቤ ደረሳቸው።

“ለ50 አመታት ከዘለቀ አምባገነናዊ አገዛዝ ነጻ ወጥቶ ሁሉን አቀፍ፣ ዴሞክራሲያዊ አስተዳድር የመመስረቻው መንገድ ከባድ ነው። እኛም 50 ዓመታት በጭቆና ኖረናል። መጀመሪያ ጀርመኖች፤ ከዚያ ኮሚኒስቶች። የቬልቬት አብዮት ከተሳካ ከ22 ዓመታት ቢያልፉም አሁንም የፈለግንው ቦታ አልደረስንም።”

በዚህ የመታሰቢያ ስነስርዓት ላይ የኢትዮጵያዋ አን ሳን ሱቺ በመባል ወደ መድረክ የተጠሩት ለዴሞክራሲ በሚሰራው National Endowment for Democracy ጥናት በማድረግ ላይ ያሉት ኢትዮጵያዊት ተቃዋሚና የዴሞክራሲ አቀንቃኝ ብርቱካን ሚደቅሳ፤ የኢትዮጵያን ጉዳይ ከአለም አቀፍ ሁኔታዎች ጋር በማጣቀስ ንግግር አድርገዋል።

ወይዘሪት ብርቱካን የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲን በምርጫ 97 ከመሩ በኋላ ለሁለት አመት ያህል በታሰሩበት፤ ቆይቶ ደግሞ የይቅርታ ወረቀታቸው ተቀዶ ለብቻቸው በታሰሩትበ ወቅት፤ ተስፋ ይሰጣቸው የነበረው የቫትስላቭ ሃቨል ጽሁፎች እንደሆኑ ያስታውሳሉ።

“ጉልበት የሌላቸው ህዙሃን ሃይል The powerof the Powerless በሚል ቫትስላቭ ሃቨል የጸፉት መጽናኛና መበረታቻዪ ነበር። ነጻና የተከበረ የሰው ይህወት ለመምራት ያለኝን ቁርጠኝነት አጠንክሮታል። አንድ ግለሰብ ጭቆናን እምቢ ሲል፤ የሚያሳልፈው መልእክት ከተሳካ አብዮት ጋር የሚስተካከል ትርጉም አለው። አንድም ሰው ሆነ ብዙ ሰዎች ያለውን ስርዓት ማንገጫገጫቸው፤ የእንቅስቃሴዎች ሁሉ የመጀመሪያ እርምጃ ነው” ብለዋል ብርቱካን ሚደቅሳ።

ወይዘሪት ብርቱካን፤ የሃቨልን የሰላማዊ አብዮትና የዴሞክራሲ ፍልስፍናዎች ከኢትዮጵያ ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታዎች ጋር አነጻጽረዋል።

“የኢትዮጵያ መንግስት የሚቃወሙትን ሁሉ ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ ብዙ ሳይተች በጭካኔ ቢያዋክብም፤ እነዚህ ተጠቂዎች ደካማና ረዳት አልባ ቢመስሉም፤ ለኔ አሸናፊዎች ናቸው። ምክንያቱም በውሸት አንኖርም ሲሉ ስርዓቱን በመቃወማቸው።”

በኢትዮጵያ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና መሰሎቹ ይፈቱ ሲሉ ወይዘሪት ብርቱካን በንግግራቸው ጠይቀዋል።

በዚህ ስነስርዓት ከኩባ ኦስዋልዶ ፓያ፣ የቀድሞ የዩናይትድ ስቴይትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማድሊን ኦልብራይት፣ ከቻይና ሊ ሻሮንግ፣ እንዲሁም ከሌሎች ለዴሞክራሲ ትግል ከሚደረግባቸው አካባቢዎች “ተቃዋሚዎች” ንግግር አድርገዋል።

ተመሳሳይ ርእስ

XS
SM
MD
LG