በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢትዮጵያ የምግብ ሸቀጦች ዋጋ በ50 ከመቶ ጨመረ


በኢትዮጵያ የምግብ ዋጋ ባለፈው አመት ሃምሌ ወር ከነበረው 50ከመቶ የሚጠጋ ጭማሪ ማሳየቱን የመንግስቱ ማእከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ስሟ እንዳይጠቀስ የፈለገችው አራት ልጆች ብቻዋን የምታስተዳድር የአሰላ ከተማ ነዋሪ ዛሬ ማርፈጃውን ገበያ ወርዳ ነበር።

“ከበርበሬ አቅም በፊት 30 እና 40 ብር የነበረው አሁን 54 እና 55 ብር ገብቷል”

በዚህ በተሰናበትንው የሃምሌ ወር የኢትዮጵያ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 40 ከመቶ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግስት የመረጃ አጠናቃሪ ቢሮ የሆነው የማእከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በዛሬውለት አስታውቋል።

ከዚህ የዋጋ ግሽበት ትልቁን ቦታ የሚይዘው በምግብ ዋጋ ላይ የነበረው ጭማሪ ነው። በዚህም መሰረት ባለፈው አመት ሀምሌ ወር ከነበረው የዋጋ ንረት የ47.4 ከመቶ ጭማሪ ታይቷል ማለት ነው።

ሸማቾች በአጠቃላይ የምግብ ዋጋ ላይ የሚታየው ንረት ኑሯቸውን እንደጎዳው ገልጸው፤ በተለይ ከመጋቢት ወር ጀምሮ ከ20እና 30 ከመቶ በላይ በየወሩ እየጨመረ የመጣው የምግብ ዋጋ በክረምቱ መባባሱ ኑሯቸውን እንደጎዳው ይገልጻሉ።

በባህር ዳር ከተማ በጉልት ችርቻሮ የምትተዳደረው አረጋሽ፤ ደምበኞቿ ዋጋ ሲጨምርባቸው ምን ያህል እንደሚቸገሩ ታውቃለች። በራሷም ኑሮ ላይ የዋጋ ንረቱ የፈጠረውን ጫና ትገልጻለች አረጋሽ።

“ሽሮ ወደ ግንቦትና ሚያዝያ ወር 18ብር የነበረው ዛሬ 25ብር ደርሷል” ብላለች አረጋሽ።

ምንም አይነት ሳይንሳዊ አሰራርን ባልተከተለ መልኩ፤ እንዲሁ በለፍ ተቀደም ያነጋገርናቸው ሸማቾች ከሚገልጹት መረዳት እንደሚቻለው በአንዳንድ መሰረታዊና በስፋት ለፍጆታ በሚውሉ ምርቶች ላይ የሚታየው የዋጋ ጭማሪ እስከ 100 እጅ ወይንም እጥፍ ይደርሳል።

በአዲስ አበባ ከተማ ዘጋቢያችን ፒተር ሃይንላይን ያነጋገረው የዘይት ቸርቻሪ መንሱር መሀመድ የሚከተለውን ብሏል።

“ውድ እንደሆነ ነው ሸማቾች የሚናገሩት። በአንድ ወቅት የአትክልት ዘይት በ20 ብር ይሸጥ ነበር፤ አሁን በሊትር ስልሳ ብር ገብቷል። የ200 እጅ ጭማሪ መሆኑ ነው። ያው ሸማቾች ከኪሳቸው ጋር ፍላጎታቸውን ያስተካክላሉ። የአትክልት ዘይት ሲወደድ የዘንባባ ዘይት መግዛት ጀምሯል”

በስልክ ከአዲስ አበባ ያነጋገርንውና ስሙን ያልጠቀሰ በግንባታ ስራ የተሰማራ ወጣት ክረምቱ ሲቃረብ የኑሮ ውድነት መከሰቱ የተለመደ ቢሆንም፤ የዘንድሮው ግን የተለየ መሆኑን ነው የሚናገረው።

በ1ሽህ 500 ብር የወር ደመወዝ የሚሰራው ወጣት ከቤተሰቦቹ ጋር እንደልጅነቱ አብሮ እየኖረም፤ ገቢው እንደማይበቃው ይናገራል። በዚህ ሳቢያ አብዛኛው ወርሃዊ ደመወዙን ለምግብና ለመጓጓዣ እንደሚያውል ገልጿል።

ሌላኛው ከፍተኛ ጭማሪ የታየበት የቤትና የመጓጓዥ ወጭ ነው። የማእከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያትተው በሁለቱ የ40 ከመቶ ጭማሪ ታይቷል።

አንድ ሊትር ቤንዚህ በ21 ብር በመሸጥ ላይ ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት በዚህ አመት በርካታ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን እንደሚያከናውንና በማከናወን ላይ መሆኑን በመግለጽ እንቅስቃሴ ሲጀምር የምጣኔ ሀብት አዋቂዎች ያስጠነቀቁት ይሄንኑ ነበር።

የአገሪቱ የምርት አቅም በእጅጉ ካልጨመረ፤ የዋጋ ንረት መከሰቱ አይቀሬ ነው ሲሉ በተደጋጋሚ አስጠንቅቀዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ አገሪቱ በምታስመዘግበው ፈጣን እድገት ግሽበትን በአንድ ዲጅት እንደሚገታ አስታውቆ ነበር።

በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ቀንድ ባለፉት 60 ዓመታት ያልታየ ድርቅ ተከስቷል። በትንሹ 4.5 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያ እርዳታ ያሻቸዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለው ኢትዮጵያ ውስጥ እርዳታ የሚያገኙ 13 ሚሊዮን ዜጎች አሉ።

በአካባቢው የተከሰተው ድርቅ ደቡብና ደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያን ለአስቸኳይ ተረጂነት ሲያጋልጥ በተለያዩ አካባቢዎች የድርቅ ስጋት እንዳለ የእርዳታ ሰራተኞች አስታውቀዋል።

በዚህ ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግስት ኢኮኖሚው በሁለት ዲጂት እያደገ ነው ይላል። የአለም የገንዘብ ድርጅት የኢትዮጵያ የቀጣዩ አመት እድገት 7.5 ከመቶ እንደሚሆን ተንብዩአል።

ተመሳሳይ ርእስ

XS
SM
MD
LG