የኢትዮጵያ መንግስት ወደ 200 የሚጠጉ የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር (ኦነግ) ታጣቂዎችን ማሰሩን ይናገራል።
እነዚህ ኦሮሚያ ክልል በጂማ፣ ነቀምቴ፣ ቡራዩ፣ ሆለታ እና ሰበታ አካባቢ የታሰሩት ሰዎች የሽብር ስራ ለማከናወን ለወራት በኤርትራ ከሚገኘው የኦነግ አንጃ ሰልጥነው መላካቸውን አንድ ከፍተኛ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣን ገጽለዋል።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት በኢትዮጵያ ሰላማዊ ፖለቲካ የሚያራምደው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን ወክለው የፓርላማ አባል የነበሩ፣ አባላትና ደጋፊዎች በጠቅላላው ወደ 64 የሚሆኑ ሰዎች መታሰራቸውን የድርጅቱ ምክትል ሊቀ-መንበር በቀለ ገርባ ተናግረዋል።
ከዚያም በተጨማሪ ተማሪዎች፣ አስተማሪዎችና የግል ባለሃብቶች ከታሳሪዎቹ እንዳሉበት ኦፌዴን አስታውቋል።
የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር ቃል-አቀባይ ዶክተር በያን አሶባ ድርጅቱ በኤርትራ መሰረት ቢሮረውም የሽብር ስራን እንደማይደግፍና የታሰሩትን ሰዎች እንደማያውቅ ገልጸዋል።
“እንደሚባለው ኤርትራ ሄደው፣ ሰልጥነው፣ ታጥቀው የሚባለው መሰረተ-ቢስ የሃሰት ወሬ ነው” ብለዋል ዶክተር በያን።
ኦነግ በኤርትራ እንደሚንቀሳቀስ የሚያምኑት ዶክተር በያን፤ ድርጅቱ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ሽብር የመፍጠር አላማ እንደሌለው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት እንዲይ ያሉ እርምጃዎችን የሚወስደው በሰሜን አፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ አምባ-ገነኖችን ከስልጣን ያወረዱና እያወኩ የሚገኙ ህዝባዊ አመጽ ይከሰትብኛል ከሚል ፍራቻ እንደሆነ ዶክተር በያን ያስረዳሉ።
የኢትዮጵያ ገዥ ፓርቲ ኢህ አዴግ በትጥቅ ትግል የደርግን ስርዓት ያሸነፈበትን 20ኛ አመት በግንቦት ወር በድምቀት ሊያከብር ተዘጋጅቷል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች አስተዳደሩ የዜጎቹን መብት በመጣስ፣ በእስራት በወከባና የተለየ አስተሳሰብ የሚያራምዱ ዜጎች በነጻናት እንዳይቀሳቀሱ ያግዳል ሲሉ፤ በተደጋጋሚ ይከሳሉ።