በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ባድመ ከተማ አቅራቢያ ከባድ የተኩስ ድምጽ እንደሚሰማና የቆሰሉ ወታደሮች በሃኪም ቤት መታየታቸውን ምስክሮች ገለጹ


ሰሜን ኢትዮጵያና ኤርትራ
ሰሜን ኢትዮጵያና ኤርትራ

ምስክሮችና ዘገባዎች በባድመ ትምህርት ቤት ተቃጥሏል ሲሉ፤ የወረዳው አስተዳዳሪ ሐሰት ብለዋል

በኢትዮጵያና ኤርትራ ሰሜን ምእራብ ድንበር ባድመ ከተማ አካባቢ የተኩስ ድምጽ መስማታቸውንና ቁስለኞች በሃኪም ቤት ሲታከሙ መመልከታቸውን አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎችና፤ በአካባቢው አባላት እንዳላቸው የሚናገሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታወቁ።

ከሳምንት በፊት ኤርትራ 21ኛ የነጻነት ቀኗን ባከበረችበት እለት የኢትዮጵያ ጦር ድንበር ተሻጋሪ ጥቃት ማካሄዱን የኢትዮጵያ የመከላከያ ምንስቴር ምንጮችን ጠቅሶ የሪፖርተር ጋዜጣ የዘገበ ሲሆን፤ በዚህ ሳምንት ማብቂያ ደግሞ በባድመ የሚገኝ አንድ ት/ቤት መቃጠሉን ጋዜጣውና ቪኦኤ ያነጋገራቸው የአይን ምስክሮች ገልጸዋል። በከተማው አንድ አውቶብስ መቃጠሉም ተዘግቧል።

በኢትዮጵያና ኤርትራ ሰሜን ምእራብ ድንበር ባድመ ከተማ አካባቢ አዲ ኮከብና አዲ ድዓሮ ቀበሌዎች እንዲሁም በባድመ ከተማ አቅራቢያ ላለፉት ሁለት ሳምንታት በምሽት የከባድ መሳሪያ ተኩስ፤ እንዲሁም የነፍስ ወከፍ ጥይት ድምጽ እንደተሰማ አንድ የአካባቢው ሰው ለዝግጅት ክፍላችን ያዩትን ገልዋል።

ሰሜን ኢትዮጵያና ኤርትራ
ሰሜን ኢትዮጵያና ኤርትራ

የአይን ምስክሩ የተኩስ ድምጽ መስማታቸውንና ቁስለኞች በሃኪም ቤት ሲታከሙ መመልከታቸውን ለቪኦኤ ገልጸዋል።

ሳምንታዊው የሪፖርተር ጋዜጣ የመከላከያ የውስጥ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ የኢትዮጵያ ጦር ባለፈው ሳምንት ድንበር ተሻግሮ የሰነዘረው ጥቃት፤ አንድ ብርጌድ የኤርትራ ጦር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ ነው ብሏል።። በጥቃቱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ባይታወቀም ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናትን ጨምሮ ወታደሮች የተማረኩበት እንደሆነ ተጠቅሷል። በኢትዮጵያ በኩል የደረሰው ጉዳት አልተገለጸም።

ከዚህ ጥቃት በኋላ በተከታታይ የሚሰሙ የተኩስ ድምጾች እንዳሉ ምስክሩ ለቪኦኤ የገለጹ ሲሆን በባድመ ከተማ የሚገኝ አንድ ት/ቤት በከባድ መሳሪያ ተመቶ መቃጠሉን ገልጸዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ከአዲስ አበባ የተሰጠ መግለጫ የለም። የኤርትራ የማስታወቂያ ሚንስትር አቶ አሊ አብዱ ለአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ “በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቢያለሁ” ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ቃል አቀባዮችን ለማግኘት ያደረግንው ጥረት አልተሳካም።

የታህታይ አዲ አቦ አስተዳዳሪ ለአከ ገ/እግዝሄር ከባድመ ከተማ ሆነው ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት መግለጫ፤ በባድም ከተማ የተቃጠለ ትምህርት ቤትም ሆነ አውቶብስ የለም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰራዊት ድንበር ተሻግሮ በኤርትራ ጦር ላይ ጥቃት ሰንዝሯል በሚሉ ዘገባዎች እንዳነበቡ ገልጸው። በአካባቢው የሰሙት የተኩስ ወይም የውጊያ ድምጽ እንዳልነበረ ለአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ገልጸዋል።

የድንበር ተሻጋሪ ጥቃቶች ሁለቱን አገሮች በሚያዋስነው ሰፊ የ1ሽህ 500 ኪ.ሜ ድንበር አልፎ አልፎ ይከሰታል። በቅርብ ጊዚያት በአፋር በኩል በጎብኝዎች በሚዘወተር ስፍራ የደረሰውን ጥቃት የኢትዮጵያ መንግስት በኤርትራ ለሚሰለጥኑ ታጣቂዎች ኃላፊነቱን ሲሰጥ፤ ኤርትራ አስተባብላለች።

በቅርብ ጊዚያት ደግሞ በምእራብ በኩል በተከዜ ወንዝ ዙሪያ አነስተኛ የወርቅ ማእድን አውጭዎች መታፈናቸውን መንግስትና ተቃዋሚዎች ይገልጻሉ። አረና ትግራይ የተቃዋሚ ፓርቲ እንደሚለው ከ259 በላይ ሰዎች በኤርትራ መንግስት ታፍነው ተወስደዋል።

የአረና ትግራይ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ገብሩ አስራት፤ ባለፈው ሳምንት ተካሄደ ስለተባለው የድንበር ተሻጋሪ ጥቃትና ስለ አፈናው የሚያውቁትን ለቪኦኤ ሲናገሩ

“ስለግጭቱ፣ ሻቢያ (የኤርትራ መንግስት) ጋር ስለሚደረገው ውጊያ ዝርዝር ነገር ያወቅንው ነገር የለም። አንዳንድ ሰዎች በአካባቢው የተኩስ ድምጽ እንደሚሰማና የተኩስ ልውውጥ እንዳለ ይናገራሉ” ብለዋል።

የዚህን ዘገባ ዝርዝርና የዓይን ምስክሮች የተናገሩትን ከዚህ በድምጽ ዘገባው ያድምጡ።

XS
SM
MD
LG