የዩናይትድ ስቴይትስ የብድር ጣራ መነሳትና አለመነሳት የሰሞኑ የመገናኛ ብዙሃን ትኩረት ሆኖ ነው የሰነበተው። የፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ አስተዳደር በበጀት መጓደል የገጠሙትን እክሎች ሊያስተካክል፤ የመንግስቱን ወጭ በመቀነስ ላይ ባለበት ወቅት፤ አገሪቱ ተጨማሪ ብድር የምታገኝበትና፤ ከዚህ ቀደመ የቆዩ ብድሮቿን ለመክፈል እንድትችል፤ ተጨማሪ ብድር የማግኘት እድሏ በህግ ቋጠሮ ተበጅቶለታል።
የባራክ ኦባማ አስተዳድር የአሜሪካ የብድር ጣራ ካልተነሳ አገሪቱ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ትወድቃለች በሚል አምርሮ በመከራከር ላይ ይገኛል። የህዝብ ተወካዮች በሚገኙበት ኮንግረስም ክርክሩ በዴሞክራቶችና ሪፐብሊካኖች ጦፏል።
ዴሞክራቶቹ ከኦባማ ጎን ተሰልፈዋል፤ ሪፐብሊካኖቹ የብድር ጣራውን አናነሳም ብለዋል።
በትናንትናውለት ፕሬዝደንት ኦባማ በዋይት ሃውስ ቤተመንግስት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ አስተዳደራቸው ከኮንግረስ መሪዎች ጋር ባደረገው ውይይት መጠነኛ እመርታዎች ቢታዩም፤ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ነገሮች እየጠበቡ መሄዳቸው እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።
ለሳምንታት የዘለቀው ክርክር በዴሞክራቶችና በሪፐብሊካኖች በይፋ በመገናኛ ብዙሃንና በዝግ በሚደረጉ ድርድሮችና ስብሰባዎችም ጭምር ሲስተጋቡ ቆይተዋል። የዩናትድ ስቴይት የነጻነት ቀን በሰኔ ወር ማብቂያ ላይ ሲከበር ፕሬዝደንት ኦባማ በብድር ጣራው ጉዳይ አስቸኳይ መፍትሄ ያሻዋል ብለዋል።
“ባለፉት አስርት አመታት ዋሽንግተን የአገሪቱን ብድር ጣራዊን ካስነካችው በኋላ፤ አሁን ተቀማጭ ገንዘባችንን መጨመር ይገባናል” ብለዋል ኦባማ።
ፕሬዝደንቱ አክለውም ሁሉንም ዘርፎች ተመልክቶ የቀረጥ እፎይታ በበጀቱ መካተት እንደሚገባውና አስተዳደራቸው ሁሉንም ተመልክቶ ገንዘብ የሚባክንባቸውን ፕሮጀክቶች በማቆም ገንዘብ እንደሚቆጥብ ገልጸዋል።
የዩናይትድ ስቴይትስ ኢኮኖሚ ከአለም የገንዘባ ውድቀት ወዲህ ከገባበት አዘቅት ለመውጣት በሚፍጨረጨርበት ወቅት፤ መንግስቱ የበጀት አለመመጣጠን ገጥሞታል፣ በዚያ ላይ የብድር ጣራው ሰማይ ነክቷል። ሪፐብሊካኖች ለዚህ ችግር መፍትሄው፤ መንግስት ወጭውን መቀነሱ ነው ይላሉ።
“የሌለንን ገንዘብ ልናወጣ አንችልም። ከዋሽንግተን የሚመጣ አንድ ዶላር ውስጥ 42 ሳንቲሙ በብድር የተገኘ ነው። ከዚህ ውስጥ 47 ከመቶው ከውጭ የተገኘ ብድር ነው፤ ቻይና ቁጥራ 1 አበዳሪያችን ናት” ብለዋል በኮንግረስ የበጀት ኮሚቴ ሊቀ-መንበር ሪፐብሊካን ፖል ራያን።
ዴሞክራቶቹ በበኩላቸው የዩናይትድ ስቴይትስ መንግስት የቀረጥ ገቢ ከ1950ዎቹ ወዲህ በጣም ዝቅ ያለ መሆኑን ይጠቅሳሉ። “በምናደርጋቸው ድርድሮች እንዳየንው፤ ሪፐሊካን ጓዶቻችን የአገሪቱን ኢኮኖሚ አዝቅት ውስጥ ማስገባት ግድ አይሰጣቸውም። እንዲያውም ባንጻሩ የቀረጥ እፎይታዎች እንዲነሱ ፈጽሞ አይፈልጉም” ብለዋል የኒውዮርኩ ዴሞክራት ሴናተር ቻርልስ ሹመር።
ሪፐብሊካኖች የመንግስትን ገቢ ለመጨመር ቀረጥ መጨመር የሚለውን አሳብ አይደግፉትም። የዩናይትድ ስቴይትስ መንግስት ያለበትን የ1.5 ትሪሊየን የበጀት መጓደል ከማሟላት ይልቅ፤ የቀረጥ ገቢው ሲጨምር ተጨማሪ ገንዘብ ያወጣል ሲሉ አጥብቀው ይከራከራሉ።
“ችግራችን ትንሽ ቀረጥ መክፈላችን አይደለም። ችግራችን የምናወጣው ገንዘብ ብዙ መሆኑ ነው” ብለዋል ሪፐብሊካኑ ሴናተር ጆን ካይል
ከዚህ ሁሉ የፖለቲካ ክርክር በኋላ አሜሪካኖች ከሀምሌ 26 በፊት ውሳኔ ማሳለፍ ይኖርባቸዋል። የብድር ጣራውን ማንሳት፤ አለማንሳት፤ የበጀት መጓደሉ እንዴት እንደሚስተካከልና የቀረጥ ጉዳይ ከዚች ቀን በፊት ውሳኔ ማግኘት ይገባቸዋል።
ፕሬዝደንት ኦባማና አስተዳደራቸው ተስፋ ሰንቀዋል። ከምርጫና ከድምጽ ማግኘት አንጻር የሚደረጉ የፖለቲካ ክርክሮች ቢበረቱም፤ በስተመጨረሻ የብድር ጣራው እንደሚነሳ እምነት አላቸው።
“ዴሞክራሲ ሁሌ የተዋበ አሰራር አይደለም። እንከራከራለን በሃሳብ አንስማማም፤ ነገር ግን በተደጋጋሚ ያረጋገጥንው ነገር ቢኖር ችግሮችን ለመፍታት አብረን እንደምንሰራ ነው። በሁሉም ጉዳዮች ላይ አይን ለአይን ባንተያይም አገራችንን እንወዳለን፣ በወደፊት ተስፋዋም የጋር እምነት አለን። ይሄንን ስሜት ነው አሁን ልናስተጋባ የሚገባን” ብለዋል ፕሬዝደንት ኦባማ።
በሴኔቱ ተቀባይነት ያላቸው ፖለቲከኞች ተሰባስበው ጉዳዮን ለመሸምገል ጥረት ይዘዋል። እነዚህ ፖለቲከኞች የመንግስቱን ወጭ ለመቀነስና ዩናይትድ ስቴይትስ ብድሯን የምትከፍልበትን መንገድ ለማመቻቸት ጥረት ይዘዋል።