በምእራብ አርሲ ዞን አሳሳ ከተማ የዓርብ ጸሎት አድርሰው ከመስጊድ በሚመለሱ ሰዎችና በፖሊስ መካከል በተፈጠረ ግጭት ቢያስ 4 ሰዎች ሲገደሉ በርካቶች ቆስለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በሃይማኖት ሽፋን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሲመሩ የነበሩ አንድ የአሳሳ ከተማ ነዋሪን የጸጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር ሲያውሉ፤ ግብረ አበሮቹ በፈጠሩት ሁከት በሰው ላይና በንብረት ጥፋት ደርሷል ብሏል።
በስፍራው የነበሩ የአይን ምስክሮች ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋለው ሰው፤ ለምን እንደሚታሰር፤ ከታሰረም መብቱ ተጠብቆ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንዲያመራ፤ ወይም የአካባቢው ማህበረሰብ ለህግ እንዲያቀርብ በጠይቁ ጊዜ ፖሊሶች ሁኔታውን ባለመቀበል ሰውየውን ሲያስሩ፤ ማህበረሰቡ በቁጣ ድንጋይ መወርወር መጀመሩን ይገልጻሉ። ለዚህ ቁጣ የፖሊስ አጸፋዊ ምላሽ ጥይት በቀጥታ ውደ ሰዎች መተኮስ እንደነበር በስፍራው የነበሩ ሰዎች ለአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ፖሊስ አዛዥ አቶ ደበሌ አዱኛ የእስልምና ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የጅሃድ ጦርነት ሲቀሰቅስ የነበረ ግለሰብን በቁጥጥር ስር ለማዋል በተደረገ እንቅስቃሴ፤ ጥቂት ግብረ አበሮቹ በፈጠሩት ሁከት 4 ሰዎች መገደላቸውንና 10 ፖሊስ መቁሰሉን አቶ ደበሌ የመንግስቱ ልሳን ለሆነው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ገልጸዋል። ከሰላማዊ ሰዎች የቆሰለውን ቁጥር ይፋ አላደረጉም።
“ይሄ ቡድን የሚያራምደው ሃይማኖት አይደለም፤ በሃይማኖት ሽፋን ድብቅ የፖለቲክ አጀንዳ ያለው ነው። ፖሊስ ባደረገው ምርመራ ያረጋገጠውም የግለሰቦቹ አላማ ይች አገር የተያያዘችውን የልማትና የእድገት ጉዞ ማደናቀፍ ነው” ብለዋል።
አቶ ደበሌ አክለውም በአሳሳ በተቀሰቀሰው ሁከት የህዝብ አገልግሎቶች ማለትም የስልክና የፖስታ ቤት ህንጻዎች ላይ ጉዳት ደርሷል። በዚህ እንቅስቃሴ ተሳትፈዋል ያላቸውን ፖሊስ በቁጥጥር ስር እንዳዋለ ገልጸዋል።
የመንግስቱን ቃልና የአሳሳ ከተማ ነዋሪዎችን የምስክርነት ቃል በዚህ ዘገባ ያዳምጡ