በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአፋር የፌዴራል ፖሊስ ሁለት ሰዎችን ከእስር ቤት አውጥተው መግደላቸውንና አንድ ማቁሰላቸውን ነዋሪዎች ገለጹ


በአፋር ክልል ዱብቲ ከተማና በሎጊያ የሰሞኑ የፌዴራል ፖሊስና የክልሉ ህዝብ ውጥረት፤ የክልሉ ነዋሪዎችና ባለስልጣንት የመወያያ ርእስ ሆኖ ነው የሰነበተው። ሁኔታው በአፋሮች ዘንድ ቁጣ መቀስቀሱን ነው፤ ከግማሽ ደርዘን የሚበልጡ አስተያየታቸውን ለአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ የሰጡ ነዋሪዎች የገለጹት።

የጸጥታ ውጥረቱ የተጀመረው እንዲህ ነው፤ በሳምንቱ መጀመሪያ አንድ የፌዴራል ፖሊስ ባልደረባ ከባለቤቱ ጋር በሚኒባስ ሲጓዝ ሁለቱም ተገደሉ።

ከዚህ ግድያ አስቀድሞ ከሁለት ሳምንታት በፊት አንድ የ17-ዓመት የአፋር ተወላጅ በፌዴራል ፖሊስ አባላት መገደሉን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል። ግድያው በተካሄደበት የሸንኮር አገዳ ልማት ጣቢያ በጥበቃ ስራ የተሰማራው ወጣት የተገደለውም ትጥቁን እንዲፈታ በፖሊስ ተጠይቆ፤ ትእዛዙን ባለመቀበሉ እንደሆነ ምስክሮች ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በሚኒባስ ሲጓዝ የነበረ የፌዴራል ፖሊስ ባልደረባ ከነባለቤቱ ከተገደለ በኋላ፤ ገዳዮቹ በበቀል ደም ለመመለስ የፈለጉ የ17-ዓመቱ ሟች ቤተሰቦች ናቸው በሚል ጥርጣሬ፤ ወዲያውኑ ከ9በላይ የቤተሰብና የጎሳ አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ።

በትናንትናውለት መገደላቸው የተረጋገጠው ሁለት ሰዎችና ክፉኛ የቆሰለው ሌላ ግለሰብ፤ በእስር ቤት የህግ እስረኛ ሆነው ሳለ፤ በጥይት ተመተው የተገደሉና የቆሰሉ ናቸው።

ሁኔታው እንዴትና መቼ አንደተፈጠረ፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ለዝግጅት ክፍላችን አብራርተዋል። ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የዱብቲ ከተማ ነዋሪ የሚከተለውን ቃል ለቪኦኤ ሰጥተዋል።

በአካባቢው የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ቁጣ ተከትሎ ከፍተኛ የፌዴራል ጉዳዮችና የፖሊስ ባለስልጣናት ወደ አፋር ተንቀሳቅሰዋል።

የአፋር ክልል ባለስልጣናት በጉዳዮ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን፤ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኢስማኤል አሊ ሴሮ ጀምሮ በተዋረድ የደህንነትና የጸጥታ ባለስልጣናትን ለማግኘት ያደረግንው ጥረት አልተሳካም።

ጥረታችንን ቀጥለን ወደ ዱብቲ ወረዳ የፖሊስ አዛዥ ደውለን ስብሰባ ላይ እንዳሉና ሊያናግሩን እንደማይችሉ ገልጸዋል። የወረዳው አስተዳዳሪም በስፍራው የለሁም፤ በመኪና እየተጓዝኩ ስለሆነ ላነጋግራችሁ አልችልም ብለውናል። ወደ ባለስልጣኑ መልሰን ብንደውልም መልስ አላገኘንም።

ቀጥለን ከምስክሮች ያገኘንውን አስተያየት እናቀርባለን። ከዚያ በፊት ግን የክልሉ ወይንም የፌዴራል ባለስልጣናት ሊመልሷቸው የሚገባቸው ጥያቄዎች አሉ።

1ኛ የህግ ታሳሪዎች ከህዝባዊ ፖሊስ እጅ ወጥተው፤ ለምን ለፌዴራል ፖሊስ አልፈው ተሰጡ? እንዴትስ በህግ ጠለላ ስር ሳሉ ተገደሉ?

2ኛ በሚኒባስ ሲጓዝ የነበረው የፖሊስ ባልደረባንና ባለቤቱን ማን እንደገደለ የሚደረገው ምርመራ በምን ሂደት ላይ ይገኛል

3ኛ ከሁለት ሳምንት በላይ የተገደለው የ17 ዓመት የአፋር ወጣት ግድያ ማጣራት በምን ላይ ይገኛል። የአካባቢው ማህበረሰብ ገዳዮ የፖሊስ ባልደረባ አሁንም በስራው ላይ ይገኛል፤ ፍትህና ተጠያቂነት ጠፍቶ፤ በወንጀል ተጠያቂ ሰው በነጻነት ይኖራል ሲሉ ያማርራሉ። እነዚህ ጥያቄዎች መልስ ያሻቸዋል። የአፋር ባለስልጣናት እንዲመልሷቸው እንጠይቃለን።

XS
SM
MD
LG