በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አሜሪካዊያኑ ሻባቦች


የአፍሪካ ሕብረት ታንኮች የሞቃዲሾ ሠፈራቸውን እየጠበቁ
የአፍሪካ ሕብረት ታንኮች የሞቃዲሾ ሠፈራቸውን እየጠበቁ

ቅዳሜ ዕለት ሞቃዲሾ ውስጥ የተጣለውን የፅንፈኛው ንቅናቄ አልሻባብ አጥፍቶ ጠፊ ፍንዳታ ያደረሰው አሜሪካዊ ዜጋ ሆኖ መገኘቱ እንዳላስገረማቸው የአፍሪካ ተንታኞች አስታወቁ፡፡

ቅዳሜ ዕለት ሞቃዲሾ ውስጥ የተጣለውን የፅንፈኛው ንቅናቄ አልሻባብ አጥፍቶ ጠፊ ፍንዳታ ያደረሰው አሜሪካዊ ዜጋ ሆኖ መገኘቱ እንዳላስገረማቸው የአፍሪካ ተንታኞች አስታወቁ፡፡

የአፍሪካ ጉዳይ አዋቆች በፅንፈኞቹ ወገን ከቆሙ አሜሪካዊያን ገና ብዙ ጥቃቶችን እንደሚጠብቁ እየተናገሩ ነው፡፡

ከከትናንት በስተያ ቅዳሜው የሞቃዲሾ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት አድራሾች አንደኛው የሆነው አሜሪካዊ አብዲሰላም የሚባል መሆኑን የአልሻባብ ወገን ናቸው የሚባሉ መገናኛ ብዙኃን እና ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ያሉ የቀድሞ ጓደኞቹ ናቸው የተናገሩት፡፡

አብዲሰላም ሁሴን አሊን ያውቁ የነበሩ ሶማሊያ-አሜሪካዊያን እንደገለፁት የተወለደው ሶማሊያ ውስጥ ሲሆን ወደዩናይትድስ ስቴትስ የመጣው ግን ገና የሁለት ዓመት ሕፃን ሆኖ ነበር፡፡

አብዲሰላም የዛሬ ሦስት ዓመት አካባቢ የት እንደገባ ሣያውቁ የተሰወረ ጊዜ በሰሜን ዩናይትድ ስቴትስ ግዛቷ ሚኔሶታ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እንደነበረ አመልክተዋል፡፡

አልሻባብ በአሥሮች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለውበታል የሚለው ጥቃት የታለመው በአፍሪካ ሕብረት የሰላም ጥበቃ ኃይሎች ላይ ነበረ፡፡ የተገደሉትን ሰዎች ቁጥርና ማንነታቸውን አስመልክቶ ግን ከነፃ አካል የተገኘ ማረጋገጫ እስከአሁን የለም፡፡

ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ የሠላም ኢንስቲትዩት ባልደረባው ዴቪድ ስሞክ ለቪኦኤ ሲናገሩ "አልሻባብ ከአደጋ ጣዮቹ አንደኛው አሜሪካዊ ቢሆን ወሬው በብዙ እንደሚገንን አውቋል" ብለዋል፡፡

ስሞክ አክለውም "ሰሚና ተመልካች ለማግኘትና አሁንም ሙሉ አቅምና ጉልበት ያለው ለማስመሰል አልሻባብ ወደ እንዲህ ዓይነት ተስፋ የመቁረጥ እንቅስቃሴዎች ይዞራል፡፡ አድራጎቱ በተጨማሪም አጥፍቶ ጠፊ ቦምብ ተሸካሚዎችን በእንዲህ ዓይነት ሁኔት መጠቀሙ አልሻባብ ከአልቃይዳ ጋር ያለው ቁርኝት ይበልጥ እየጠበቀ መምጣቱን ያሣያል፡፡" ብለዋል፡፡

የአትላንቲክ ምክር ቤቱ ፒተር ፋም ደግሞ አልሻባብ በመጭዎቹ ሣምንታት ውስጥ ሌሎችም አሜሪካዊያን ሶማሊያ ውስጥ ተጨማሪ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃቶችን ያደርሣሉ ብለው እንደሚያስቡ ዋሽንግተን ላይ ተናግረዋል፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት አሜሪካዊያኑ አልሻባብን መቀላቀላቸውን ቢያውቅ እንኳ ከአድራጎታቸው ሊያቆማቸው በእጅጉ ይከብደዋል ይላሉ ፋም፡፡

"የአሜሪካ የስለላ ተቋም ከአልሻባብ ጋር መሆናቸውን በግምት የሚያውቅ ይመስለኛል፡፡ ይሁን እንጂ በዚያ ስፋት ባለው ደቡብና ማዕከላዊ ሶማሊያ ክልል ውስጥ በትክክል የት ሊገኙ እንደሚችሉ የሚጠቁም መረጃ ግን ይኖረዋል ብዬ አላስብም" ሲሉ አክለዋል፡፡

ምንም እንኳ ድርቅና ቸነፈሩ፣ የኬንያ ወታደራዊ ጥቃትና በራሱም በአልሻባብ አመራር ውስጥ የተፈጠረው መከፋፈል ተረባርበው ንቅናቄውን በእጅጉ ያዳከሙት ቢሆንም ዛሬ በቁጥጥሩ ሥር የሚገኙ አባባቢዎችን እንደተቆጣጠረ እንደሚቆይ ፒተር ፋም አመልክተዋል፡፡

ቁጥራቸው የበዛ የሶማሊያ ዳያስፖራ አባላት ከሚገኙባት የሚኔሶታ ግዛቷ ትልቋ ከተማ ሚኔአፐሊስ የጠፉትን ሃያ ወጣቶች ጨምሮ ሰላሣ ሶማሊያ አሜሪካዊያን አልሻባብን ሶማሊያ ውስጥ ለመቀላቀል መሠወራቸውን የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት ይናገራሉ፡፡

የዋሽንግተኑ ሥልታዊና ዓለምአቀፍ ጥናቶች ማዕከሉ ሪቻርድ ዳውኒ ደግሞ በአልሻባብ ገንዘብ ማሰባሰቢያ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የሚሣተፉ አሜሪካዊያን መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

"ጥቂት ሴቶች ለአልሻባብ ገንዘብ ልካችኋል በሚል ተከስሰው (በወሩ መጀመሪያ አካባቢ መሆኑ ነው) የጥፋተኛነት ብይን ተላልፎባቸዋል፡፡ አልሻባብ ለአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት የመደባቸው ሦስት አሜሪካዊያን አሉ የሚል የግምት ጭምጭምታም ሲሰማ ነበር፡፡ የሚያሰጋው ነገር ይኼው ነው" ብለዋል ዳውኒ፡፡

በዚህ ጉዳይ ውስጥ የሚነሣው ገንዘብ አሥር ሺህ ዶላር እንደማይሞላ በሰሜን ካሮላይና ዴቪድሰን ኮሌጅ ውስጥ የሚሠሩት የሶማሊያ ጉዳዮች አጥኚ ኬን ሜንክሃውስ ተናግረዋል፡፡ አሜሪካ ውስጥ ለአልሻባብ ሰው የመመልመልና ገንዘብ የማሰባሰብ ሥራ በአዘአ ከ2 ሺህ 8 ወዲህ በእጅጉ መቀነሱን ሜንክሃውስ አመልክተዋል፡፡

ንቅናቄው በዩናይትድ ስቴትስ ይደገፍ የነበረው የኢትዮጵያ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ሶማሊያ ውስጥ ይካሄድ በነበረባቸው በሁለት ሺህ ስድስት እና በሁለት ሺህ ስምንት ዓመታት መካከል ተቀባይነቱ ገንኖ እንደነበረና ከዚያ በኋላ ግን በሶማሊያዊያኑ በራሣቸው መካከል የተነሡ ግጭቶችና መቆራቆዝ ከቸነፈሩ ጋር ተዳምረው ቀደምትና እጅግ የቀረቡ የሚባሉ ደጋፊዎቹ ፊታቸውን እንዲያዞሩበት ያስገደዳቸው መሆኑን አጥኚው ገልፀዋል፡፡

አሁን አልሻባብ ገንዘብ የሚያገኘው ከከሰል ሽያጭና ከቀረጥ ነው ይላሉ ሜንክሃውስ፡- "በ2007 እና በ2008 ዳያስፖራው ገንዘብ በገፍ አዋጥቷል፡፡ ያ ድጋፍ ግን ሶማሊያ-አሜሪካዊያን እና በሌሎችም ሃገሮች የሚኖሩ ሶማሊያዊያን በአልሻባብ እና እየወሰዳቸውም ባሉ እርምጃዎች ከተሰላቹና ካጠሉት በኋላ ደርቋል፡፡

ኬን ሜንክሃውስ ግን አንድ ማስጠንቀቂያ አላቸው፡፡ ለድንበር ዘለል ጠለፋዎቹ ምላሽ የሆነው የኬንያ ወታደራዊ ጥቃት፣ የአሜሪካ ድሮኖች ድብደባና ምናልባት የኢትዮጵያ ጦር መመለስ ጉዳይ የአልሻባብን ዝና ዳግም እንዳያገንነውና የገንዘብ ማሰባሰቡ፣ ምልመላው ተመልሶ እንዳያንሠራራ ይሠጋሉ፡፡ በዚህ አልሻባብ ድንገት ተመልሶ አንገቱን ሊያቀና ይችላል ይላሉ ሜንክሃውስ፡፡

አልሻባብ (የስሙ ትርጉም "ወጣቱ" የሆነ) በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በአሜሪካ የሚደገፈውን የሶማሊያ መንግሥት በኃይል ጥሎ አክራሪ እሥላማዊ መንግሥት ለመመሥረት ብረት ያነሣና ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚናገር ዩናይትድ ስቴትስ በሽብር መዝገብ የጣፈችው ሶማሊያዊ አማፂ ቡድን ነው፡፡

ዘገባውን ያዳምጡ፡፡

ተመሳሳይ ርእስ

XS
SM
MD
LG