አሜሪካ በካናዳ እና ሜክሲኮ ላይ የ25 በመቶ ታሪፍ ለመጫን መወሰኗ እና ሁለቱ ሃገራትም በምላሹ ተመሳሳይ ርምጃ እንደሚወስዱ ማስታወቃቸው፣ እንዲሁም ቀድሞውንም በቻይና ላይ ተጭኖ የነበረውን 10 በመቶ ታሪፍ ጨምሮ፣ በዓለም የንግድ ጦርነትና የኢኮኖሚ ቀውስ ይከሰታል የሚል ከፍተኛ ስጋት አሳድሮ ነበር። ፕሬዝደንት ትረምፕ አዲሱ ደንብ ተግባራዊ ከመሆኑ አንድ ቀን ቀደም ብሉ፣ ከካናዳ እና ከሜክሲኮ መሪዎች ጋራ መነጋገራቸውን ተከትሎ፣ ነገሮች ወደነበሩበት የተመለሱ መስለዋል።
ትረምፕ ከመሪዎቹ ጋራ ከተነጋገሩ በኋላ ሁኔታዎችን ለማጤን ተጨማሪ 30 ቀናት እንደሚወስዱ አስታውቀዋል።
ካናዳን በተመለከተ በሰሜኑ የአሜሪካ ድንበር ላይ ቁጥጥር ለማድረግ መስማማቷን፣ በአሜሪካ የበርካቶችን ሕይወት በመቅጠፍ ላይ ያለውና ፈንትነል የተሰኘው ሱስ አሲያዥ መድኃኒት በሕገ ወጥ መንገድ የሚገባበትን ሁኔታ ለማስቆም፣ ለዚህም 1.3 ቢሊዮን ዶላር በመመደብ እንድሚንቀሳቀሱ የካናዳው ጠቅላይ ምኒስትር ጀስቲን ትሩዶ መስማማታቸውን ትረምፕ አስታውቀዋል። በአዲስ ሄሎኮፕተሮች፣ ቲክኖሎጂ እና የሰው ኅይል በመታገዝና ከአሜሪካ ጋራ በመተባበር የፈንትነል ዝውውርን ለመግታት እንደሚሰሩም ተስማምተዋል። 10 ሺሕ የሚሆን የሰው ኃይል እንደምታሰማራና የፈንትነል ጉዳይ አማካሪ በመሾም ለ24 ሰዓታት ድንበሩን እንደምትቆጣጠር እንዲሁም የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪዎችንም በሽብርተኝነት እንደምትፈርጅ ካናዳ ተስማምታለች ተብሏል፡፡
በተመሳሳይም ከሜክሲኮ ፕሬዝደንት ክላውዲያ ሼይንቦም ጋራ በተደረገው ውይይት፣ 10ሺሕ ወታደሮችን በድንበር ላይ ለማሰማራት ፕሬዝደንቷ መስማማታቸውን እነዚህም ወታደሮች የፈንትለልና የሕገ ወጥ ፍልሰተኞችን ዝውውርን ለመቆጣጠር እንደሚሰሩ ትረምፖ አመልክተዋል።
በውይይቶቹም በካናዳ እና ሜክሲኮ ላይ ሊጣል የነበረው 25 በመቶ ታሪፍ፣ እንዲሁም ሃገራቱ በአጸፋው በአሜሪካ ላይ ሊጥሉት የነበረው ተመሳሳይ የታሪፍ መጠን ለጊዜው ለሰላሳ ቀናት ያህል እንዲቆም ስምምነት ላይ ተደርሷል።
በቻይና በኩል ያለው የንግድ ውዝግብና የታሪፍ ጭመራ ግን እንደቀጠለ ነው። ቻይና ለፕሬዝደንት ትረምፕ የታሪፍ እርምጃ አጸፋ ሰጥታለች፡፡ የህም ከአሜሪካ በሚገቡ በርካታ ሸቀጦች ላይ የሚጣል ሲሆን፣ በተለይም በተፈጥሮ ጋዝ ውጤቶች ላይ 15 በመቶ፣ በድፍድፍ ነዳጅ ላይ ደግሞ የ10 በመቶ ታሪፍ እንደምትጭን አስታውቃለች፡፡ አዲሱ የታሪፍ እርምጃም ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ቻይና አስታውቃለች። “የአሜሪካ የታሪፍ ጭማሪ ከዓለም ንግድ ድርጅት ደንቦችን የጣሰ እንደሆነ” ያስታወቀችው ቻይና “በአሜሪካ የሚይታዩ የኢኮኖሚ ችግሮችን ለፍታት የማይጠቅም” ብቻ ሳይሆን፣ በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን የኢኮኖሚና የንግድ ትብብር የሚጎዳ እንደሆነ ገልጻለች፡፡
በተጨማሪም የአሜሪካንን የታሪፍ ጭማሪ በተመለከተ በዓለም የንግድ ድርጅት መድረክ ላይ እንደምትሞግት ቻይና አስታውቃለች፡፡
መድረክ / ፎረም