በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አምባሳደር ጃኮብሰን የሰላም ሥምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲደረግ ጠየቁ


በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ አምባሳደር ትሬሲ ጃኮብሰን
በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ አምባሳደር ትሬሲ ጃኮብሰን

በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ አምባሳደር ትሬሲ ጃኮብሰን ኢትዮጵያ በቅርቡ የተፈራረመችውን የሰላም ሥምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንድታደርግ እና ሁሉም ወገኖች ሰብዓዊ እርዳታ ያለምንም እንቅፋት እንዲዳረስ፣ ለሲቪሎች ጥበቃ እንዲደረግ፣ መሰረታዊ አገልግሎቶች እንዲመለሱ እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት መርማሪዎች በግጭት የተጎዱ አካባቢዎች ማግኘት እንዲችሉ እንዲያመቻቹ ጠየቁ።

አምባሳደር ጃኮብሰን ይህን ጥሪ ያቀረቡት በኦሮምያ ክልል፣ ጅማ ከተማ ጉብኝት ባደረጉበት እና 'ጅማ እና አሜሪካ ኮርነር' የተሰኘውን የባህል ልውውጥ እና የትምህርት ማዕከል በድጋሚ በከፈቱበት ወቅት ነው።

ኢትዮጵያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ዛሬ ባወጣው መግለጫ በኦሮምያና በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ያለውን ፀጥታና መረጋጋት በተመለከተ፣ አምባሳደር ጃኮብሰን መሰረታዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶችን የመፍታት አስፈላጊነትን ማሳሰባቸውን አመልክቷል።

አምባሳደሯ በጅማ በነበራቸው ቆይታ ከአካባቢው አመራሮች ጋር መገናኘታቸውን እና ዩናይትድ ስቴትስ በአካባቢው ባላት ተሳትፎ፣ የረጅም ግዜ አጋርነትን ለማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች እና ሰላምን በጋር የማራመድ ጥረቶች ላይ መወያየታቸውንም የኤምባሲው መግለጫ አመልክቷል።

መግለጫው አክሎ አምባሳደር ጃኮብሰን ከጅማ ዩኒቨርስቲ ጉብኝት ማድረጋቸውን እና አሜሪካ እና ኢትዮጵያ በከፍተኛ ትምህርት ዙሪያ የበለጠ መተባበር እና አጋር ሆነው መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ጀማል አባፊታ ጋር መወያየታቸውን ጠቅሷል።

አምባሳደሯ ከሀይማኖት መሪዎች ጋርም መገናኘታቸው እና በአሜሪካ እና ኢትዮጵያ መካከል ያለው ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ግንኙነት እንዴት የበለጠ ማጠናከር እንደሚቻል የተነሱ ሀሳቦችን ማዳመጣቸውም ተጠቅሷል።

XS
SM
MD
LG