ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈፀመችውን ወረራ እንዲያወግዝ በቅርቡ ተጠርቶ በነበረው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ብዙ የአፍሪካ ሃገሮች በተአቅቦ ማስመዝገባቸው “ሃገሮቹ ከማንም ጋር አለመወገናቸውን የሚያሳይ ቢሆንም በዚህ ጉዳይ ገለልተኛ መሆን እንደማይቻል” በድርጅቱ የዩናይትድ ስቴትስ ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ አስታወቁ።
አምባሳደሯ ዛሬ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የሩሲያን ወረራ መዘዝ አፍሪካዊያኑ ሃገሮች እንዲገነዘቡት ለማድረግ ተጨማሪ ጥረቶችን እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
“[ሃገሮቹ] ያንን አቋም መያዛቸው መብታቸው ቢሆንም ሁኔታውን ከዓለምአቀፍ ሥርዓት አኳያ መመልከትም ትክክለኛው አካሄድ ነው” ብለዋል አምባሳደር ቶማስ-ግሪንፊልድ።
“ይህ ቀዝቃዛ ጦርነት አይደለም - ብለዋል አምባሳደሯ - በአሜሪካና በሩሲያ ወይም በምዕራቡና በሩሲያ መካከል ያለ ፉክክርም አይደለም።”
አምባሳደር ቶማስ-ግሪንፊልድ በመቀጠልም “ይህ ሩሲያ በጎረቤቷ ላይ የከፈተችው ጥቃት ነው፤ ሩሲያ በመንግሥታቱ ድርጅት አስኳል እሴቶች ላይ የፈፀመችው ጥቃት ነው፤ እየተጋፈጥን ያለነው ዩክሬን ላይ ከፈፀመችው ጥቃት ጋር ነው” ብለዋል።
“በዩናይትድ ስቴትስና በሩሲያ መካከል ያለ ወረራ ጦርነት አይደለም” ሲሉ አምባሳደሯ አሳስበዋል።
በጠቅላላ ጉባዔው ከተመዘገበው የተአቅቦ ድምፅ ግማሽ ያህሉ የአፍሪካ ሃገሮች ነው።
በአምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ የቢቢሲ ቃለምልልስ ላይ የተዘጋጀውን ዝርዝሩ ዘገባ ይዘን እንመለሳለን።