አል-ሸባብ በካምፓላ፥ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍፃሜ ውድድሮችን በቴሌቪዥን ሲከታተሉ ከነበሩ መካከል ከ 70 የሚበልጡ ሰዎች የተገደሉበት የቦንብ ጥቃት «የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ፣” እንደማይሆን ዝቷል።
እንደሚታወቀው፥ አሚሶም በመባል ለሚጠራው ለሱማልያው የአፍሪቃ ህብረት የሰላም ጥበቃ ተልዕኰ ወታደሮቿን ያዋጣች የመጀመሪያዋ ሀገር ዑጋንዳ ናት። የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ሙስሊም አክራሪዎቹን ከሥልጣን ካባረረ በኋላ መዲናዋን በማረጋጋት እንዲረዱ የተላኩት የመጀመሪያዎቹ የዑጋንዳ ወታደሮች ሞቃዲሾ የደረሱት እ አ ዘ አ በሰኔ ወር 2007 ዓ ም ነው።
ዛሬ በሞቃዲሾ ከዑጋንዳና ቡሩንዲ የተላኩ 6,100 የሚሆኑ ወታደሮች፥ የከተማይቱን አውሮፕላን ማረፊያ፥ ወደቡን፥ ቪላ ሱማልያ እየተባለ የሚጠራውን፥ በተ መ ድ የሚደገፈውን የፌዴራሉን የሽግርር መንግሥት አንጋፋ መሪዎች መኖሪያ ጨምሮ፥ ሌሎች ቁልፍ ተቋማት ይጠብቃሉ።
አል-ሸባብ ላለፉት ሦስት ዓመታት፥ ሞቃዲሾ ከተማ ውስጥ የቀሩትን ጥቂት ቀበሌዎች ለመቆጣጠር ባብዛኛው ከአሚሶም ጋር የተካሄዱ ውጊያዎችን መርቷል። በነዚህ ውጊያዎች ከ 50 በላይ የሰላም አስከባሪዎች እና በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎች ተገድለዋል። ዓለምአቀፍ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ጥብቅና የቆሙ ቡድኖች፥ በንጹሃኑ ሲቪሎች መገደል ሁሉንም ተፋላሚ ወገኖች ያወግዛሉ።
ዑጋንዳና ቡሩንዲ ለአፍሪቃው ህብረት በሱማልያ ተልዕኰ ወታደሮች ማዋጣታቸውን በመቃወም ጥቃት እንደሚያደርስ አል-ሸባብ ከዚህ ቀደምም አስጠንቅቆ እንደነበር ይታወሳል።
በምዕራባውያን የሴኩሪቲ ተንታኞች እምነት ግን፥ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው አልሻባብ፥ ይህኛውን አዲሱን ማስጠንቀቂያውን እንዲያውጅ ያደረገው፥ በቅርቡ ተጨማሪ 2,000 ሺህ ወታደሮች ወደ ሱማልያ እንዲላኩ በኢጋድ አባል አገሮች መሪዎች የተደረሰው ስምምነት ነው።
በዚያ ስምምነት ላይ፥ አሁን ያሉትን ለማጠናከር ከሚላኩት ወታደሮች ሁሉንም ባይሆን አብዛኞቹን፥ ሀገራቸው ለማዋጣት ፍቃደኛ መሆኗን ቃል የገቡት የዑጋንዳው ፕሬዘዳንት Yoweri Museveni የአፍሪቃ ህብረት አባል ሀገሮችም ባፋጣኝ ተጨማሪ 20 ሺህ ወታደሮችን ወደ ሱማልያ እንዲልኩ ጥሪ አቅርበዋል።
አል ሻባብ ተስፋ የሚያደርገው፥ በካምፓላ ነዋሪዎች ላይ ጥቃቱን ካነጣጠረ፥ የዑጋንዳው መሪ የገቡትን ቃል ለመሰረዝና ቀድሞ የተላኩትን ወታደሮችም ከሱማልያ ለማስወጣት ይገደዳሉ የሚል እንደሆነ የሴኪዩሪቲ ጠበብት ያስረዳሉ።
ጐዳኒ የካምፓላውን የቦምብ ጥቃቶች ያካሄደው፥ “ሳሌህ ነባሃን” የተባለው የጦር ክፍል ነው ሲል ትላንት የሰጠው መግለጫ፥ የቡድኑ እንቅስቃሴ ባብዛኛው፥ አልቃይዳ ባሰለጠናቸው ባዕዳን እየተመራ ለመሆኑ ፍንጭ ሰጥቷል።
የአሸባሪው ቡድን መሪ በዚያ መግለጫው፥ በዑጋንዳ የቦንብ ጥቃቶቹን የፈጸሙትን የጦር ክፍሉን አባላት አመስግኗል።
“ሳሌህ ነባሃን” መጠሪያውን ያገኘው፥ ነባሃን ከተባለው በትውልድ ኬንያዊ ከሆነውና ባለፈው ዓመት መጀመሪያ ላይ ከፍተኛ የአልሻባብ መሪ ከተደረገው የአልቃይዳ ነውጠኛ ነው። ከ 1998ቱ የኬንያና ታንዛኒያ የአሜሪካ ኤምባሲዎች አሸባሪ የቦንብ ጥቃቶች ጋር በተያያዘ ሲታደን የቆየው ነባሃን እ አ አ በ 2009 መስከረም ወር ላይ በዩናይትድ ስቴትስ ልዩ ኃይሎች፥ ሱማልያ ውስጥ ተገድሏል።
አል-ሸባብ በቡሩንዲም ላይ ሌላ አዲስ ማስጠንቀቂያ ያወጣ ሲሆን ቡድኑ ዋና ከተማዋን ቡጁምቡራን ዒላማ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ ብሏል።