በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአልሻባብ ታጣቂዎችና የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ተጋጩ


የአልሻባብ ታጣቂዎችና የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ተጋጩ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:52 0:00

የአልሻባብ ታጣቂዎችና የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ተጋጩ

አልሻባብ በኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ በሚገኙ ከተሞች ላይ ጥቃት ማድረሱ ተዘገበ። በአልሻባብ ታጣቂዎችና በኢትዮጵያዊያኑ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት መካከል በተካሄደ ውጊያ ከሁለቱም ወገን ወደ 80 ሰው መገደሉን ከሁለቱም ወገኖች የወጡ መረጃዎች ጠቁመዋል።

በሶማሊያና በኢትዮጵያ ድንበር ላይ በሚገኙ ዪድ እና አቶ የሚባሉ ሁለት የሶማሊያ ከተሞች ውስጥ የአልሻባብ ታጣቂዎች ትናንት ረቡዕ ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ አካባቢውን እየጠበቁ መሆናቸው ከሚነገረው የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ጋር መዋጋታቸው ተዘግቧል።

የአካባቢው ባለሥልጣናትም አልሻባብ በሶማሊያ ደቡብ ምዕራባዊ ባኩል ክፍለሃገር የወሰን አካባቢ ለረጅም ጊዜ በሠፈሩት የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ አባላት ላይ ጥቃት መክፈቱን ለቪኦኤ የሶማሊኛ አገልግሎት አረጋግጠዋል።

በውጊያው ከኢትዮጵያዊያኑ የፖሊስ አባላት 17 ከአል ሻባብ ወገን 63 ታጣቂዎች መገደላቸውን ሮይተርስ ሥፍራው ላይ እንዳናገራቸው የጠቆመ አንድ የኢትዮጵያ ፀጥታ አዛዥ ተናግረዋል።

የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ አካል የሆኑት የኢትዮጵያ መከላከያ ወታደሮች ሶማሊያ ውስጥ ከሃገሪቱ ጦር ጎን ተሠማርተው ባሉበት ጊዜ የድንበርና የአቅርቦት መሥመሮች ደኅንነት ጥበቃውን የሚያካሂዱት የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ ኃይሎች መሆናቸውን የሶማሊኛ ዝግጅት ክፍላችን ዘገባ አውስቷል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የሶማሊያ የፀጥታ ባለሥልጣን ለቪኦኤ በሰጡት ቃል አልሻባብ መጀመሪያ አቶ ከተማ የሚገኝ የኢትዮጵያ ልዩ ፖሊስ ካምፕን ማጥቃቱንና ታጣቂዎቹ አስከትለው ሰማንያ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ዪድ ከተማ ውስጥ ሌላ የልዩ ፖሊስ ኃይል ሠፈር ውስጥ ገብተው ጥቃት መክፈታቸውን ተናግረዋል።

ከዚያም የአልሻባብ ተዋጊዎች ዋሻቆ የምትባል ሌላ የሶማሊያ መንደር በአዳፍኔ የደበደቡ ሲሆን ያን ያደረጉት ልዩ ፖሊስ ተጨማሪ ኃይል ወደ አካባቢው እንዳይልክ ለማደናቀፍ ሳይሆን እንደማይቀር ዘገባው አውስቷል።

ትናንት በአካባቢው በአብዛኛው የስልክ አገልግሎት ተቋርጦ እንደነበር ዘገባው ጠቁሟል።

የአልሻባብ ቃል አቀባይ አብዱላዚዝ አቡ ሙሳብ ለቪኦኤ በሰጠው ቃል “ተዋጊዎቻችን ዪድ እና አቶ ከተሞች ተቆጣጠረዋል” ቢልም ለመገናኛ ብዙኃን እንዲናገሩ ሥልጣን እንዳልተሰጣቸው በመጠቆም ስማቸው እንዳይገለፅ ጠይቀዋል ብሎ ሮይተርስ የጠቀሳቸው በሥፍራው ያሉት ኢትዮጵያዊ አዛዥ ከአጥቂዎቹ ላይ በርካታ መሣሪያ መማረካቸውንም ተናግረዋል።

አዛዡ አክለው አልሻባብ ኢትዮጵያ ውስጥ የራሱን ክፍሎች ለማቋቋም ሠርጎ ገብቶ እንደነበረም ጠቁመዋል።

በግጭቶቹ ደርሰዋል የተባሉትን ጉዳቶች ከሦስተኛ ወገን ማጣራት አለመቻሉን ሮይተርስ አክሎ ዘግቧል።

የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዛ አብዲ ባሬ ባኮል ሚገኝበት የሶማሊያ ደቡባዊ ምዕራብ ክልል ፕሬዚዳንት ጋር መነጋገራቸውን ፅህፈት ቤታቸው ማስታወቁን ያመለከተው ሮይተርስ የክልሉ ፕሬዚዳንት ግን አስተያየት አለመስጠታቸውን ገልጿል።

XS
SM
MD
LG