የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ፍሮንሷ ፊሎን ሀገራችው ከአል-ቃይዳ ጋር ጦርነት ላይ መሆንዋን በፈረንሳይ ራድዮ ተናግረዋል።
የፈረንሳዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቤርናር ኩችነር ይኽው ቡድን የውጭ ሰዎች ጠለፋና አልፎ አልፎም ግድያ የሚፈጽምበት ወደሆነው ወደምዕራብ አፍሪካ ጉብኝት ሲያካሂዱ ቆይተዋል። ቡድኑ ፈረንሳዊውን የረደኤት ሰራተኛ ሚሼል ዤርማኖን ገድለነዋል ሲል ባለፈው ዕሁድ አስታውቋል። ያስታወቀውም የፈረንሳይና የሞሪታንያ ኃይሎች በማሊ በረሃ ካሉት ይዞታዎቹ አንዱን ወርረው ካጠቁ በኋላ ነው።
ትናንት ማክሰኞ ቤርናር ኩችነር ከማሊ ፕሬዚደንት አማዱ ቱማኒ ጋር ተገናኝተው የጋራ ፈጥኖ ደራሽ ጸረ ሽብርተኛ ኃይል ማቋቋምን ጨምሮ በበርካታ ሴኩሪቲ ነክ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል ።
በሌላ በኩል የአልጄሪያ ባለስልጣናት በዚህ ሳምንት በኡጋንዳ ካምፓላ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ሲናገሩ በሰፊውና በአመዛኙ ህግ አልባ በሆነው በሰሜናዊ ምስራቁ የአፍሪካ ክልል በምናካሂደው ጸረ ሽብርተኛ ትግል ደካማዋ አስጠቂ ማሊ ነች ማለታችው ተዘግቧል። በበረሃው የሚኖሩ አልጄሪያውያን በየመንደራቸው የየራሳቸውን መከላከያ ሚሊሽያ እንዲያያቋቁሙ መመሪያ ሰጥተናል ሲሉም ባለስልጣናቱ ተናግረዋል።
የአፍሪካ ሴኩሪቲ ተንታኝ የሆኑት ፒተር ፋም ፈረንሳይ እየወሰደች ያለው ርምጃ አይገርመኝም ይሉና ክፋቱ የስላማዊው ማግረብ አልቃይዳ በቀጣዮቹ ወራትም መተናኮሉ አይቀርም በማለት ስጋታቸውን ይገልጣሉ።
በዚህ ሳምንት በካምፓላ የተካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔም ባመዛኙ ያተኮረው በሽብርተኝነቱ ስጋት እና በሶማሊያ የሚገኝን የሰላም ጥበቃ ኃይል ማጠናከር ስለሚቻልበት ሁኔታ ነበር።
መሪዎቹ ሁለት ሺህ ተጨማሪ ወታደሮችን ለመላክ ወስነዋል። ሰላም እስከባሪዎቹም ህይወታቸው ላይ ጥቃት ከተቃጣባቸው እንዲተኩሱ ፈቃድ ሰጥተዋል።
በቅርቡ በኡጋንዳዋ መዲና በርካታ ሰዎች የተገደሉበትን የቦምብ ጥቃት ያደርስኩ እኔ ነኝ ያም የኡጋንዳ ወታደሮች ሶማሊያ መግባተትን ለመበቀል ነው ሲል አል-ሸባብ አስታውቋል። ሶማሊያ ውስጥ ሰላም አስከባሪዎቹ አዘውትረው ንጹሃን ሲቪሎች ላይ ይተኩሳሉ የሚል ስሞታ ይቀርብባቸዋል እል-ሸባብም በኡጋንዳ እና በሌላዋ ሰላም እከባሪ በላከቸው በቡሩንዲ ላይ ጥቃት ማድረሳችንን እንቀጥላለን ሲል ዝቷል።
ተንታኝ ፒተር ፋም ታዲያ ለዚህ ሁኔታ ወታደራዊ መፍትሄ ይኖርል ብለው እንደማያምኑ ነው የሚናገሩት። ተጨማሪ ሰላም አእከባሪ መላኩ ሁኔታውን ያባብሰዋል ይላሉ።
አልሸባብ የተጠናከረው እኮ ይላሉ የአፍሪካ ሴኩሪቲ ተንታኙ በባዕዳን ጣልቃ ገብነት ምክንያት ነው። ይልቁንስ የሚያዋጣው በጣም አክራሪ ያልሆኑትን አባላት ከውስጡ እየመረጡ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መስራቱ ነው በማለትም ያሳስባሉ።
የኡጋንዳው የቦምብ ጥቃት ከደረሰ ወዲህ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ሀገራቸው ለአፍሪካ ሽብርተኝነትን መዋጊያ የምትሰጠውን ርዳታ ዕጥፍ እንደምታደርግ እስታውቀዋል። የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት ለሶማሊያ የሽግግር መንግስት ካሁን ቀደም ለጦር መሳሪያ መግዣና ለወታደሮቹ ደመወዝ የሚከፍልበት በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ሰጥቷል።
የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት የቀጣዩ እኤአ የሁለት ሺህ አስራ አንድ ዓመተ ምህረት ለአፍሪካ የሴኩሪቲ ርዳታ መርሃ ግብሮች ባቀረበው የበጀት ዕቅድ ውስጥ ለአፍሪካ መንግስታት ለመሳሪያ ሽያጭ ፥ ለወታደራዊ ስልጠናና ጸረ ሽብርተኛ ፕሮግራሞች ከሰማኒያ ሚሊዮን ዶላር በላይ መመደቡ ይነገራል።