በአልጄሪያ የሚገኝ ፍርድ ቤት 49 ሰዎች ላይ ዛሬ የሞት ቅጣት አስተላልፏል።
ተከሳሾች ለዚህ የበቁት ባለፈው ነሐሴ የተከሰተውን የዱር እሳት በሃሰት ልኩሰሃል በሚል አንድን ወጣት በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደላቸው ነው።
ፍርድ ቤቱ በተጨማሪም ሌሎች 28 ተከሳሾች ላይ ከሁለት ዓመት እስከ አስር ዓመት ካለ አመክሮ የሚፈጸም የእስር ቅጣት አስተላልፏል።
ሰሜናዊቷ የአፍሪካ አገር በእአአ 1993 የመጨረሻውን የሞት ቅጣት ተፈጻሚ ካደረገች በኋላ፣ ከዛ ወዲህ ተግባራዊ እንዳይሆን አግዳለች።
ጥፋተኛ የተባሉት ግለሰቦች የ38 ዓመቱን ወጣት ጃሜል ቤን እስማኤል ቀጥቅጠው ከገደሉ በኋላ፣ በድኑን በእሳት አቃጥለዋል::
የሥነ-ጥበብ ባለሙያ የሆነው ወጣቱ ጃሜል ቲዚ ኡዙ ወደተባለው ክልል ያቀናው በተቃራኒው እሳቱን ለማጥፋት የሚካሄደውን ጥረት ለማገዝ እንደ በጎ አድራጊ ነበር።
የዱር እሳቱን በመጫር መጠርጠሩን በማወቁ ግን ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ ሪፖርት አድርጓል። ከዛም በጅምላ ተጨፍጭፎ በድኑ በእሳት ጋይቷል።
የዱር እሳቱ የ90 ሰዎች ሕይወት መቅጠፉ ታውቋል።
የልጃቸው ህይውት በዘግናኝ ሁኔታ ቢጠፋም፣ አባቱ ኑረዲን ቤን እስማኤል አልጄሪያውያን እንዲረጋጉና ወንድማማችነትን እንዲያሳዩ ጥሪ በማድረጋቸው አድናቆትን አትርፈዋል።
የዱር እሳቱ የተነሳው በወቅቱ በነበረው ከፍተኛ ሙቀት ምክንያት ነው ተብሏል።
ባለሥልጣናት ግን በእሳት ወንጀል ፈጻሚዎችንና ሌሎች ወንጀለኞችን እንደሚጠረጥሩ የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል።