ከሁለት ዓመታት በፊት በአልጄሪያ በተከሰተና የ90 ሰዎችን ሕይወት በቀጠፈ የእሳት አደጋ ወቅት፤ እሳቱን ለማጥፋት ሲሞክር የነበረን ግለሰብ፣ ‘እሳቱን ያስነሳው እርሱ ነው’ በሚል በእሳት አቃጥለው ገድለዋል የተባሉ 38 ግለሰቦች በሞት እንዲቀጡ ፍርድ ቤት ወስኗል።
የ38 ዓመቱን ቀለም ቀቢ ጃሜል ቤን ኢስማኤል እሳቱን በማስነሳት መጠርጠሩን ሲያውቅ ራሱን ለፖሊስ አሳልፎ ሰጥቶ ነበር። በስፍራው የተሰበሰቡ ሰዎች ግን ከፖሊስ መኪና ውስጥ አውጥተው ከደበደቡት በኋላ በእሳት አቃጥለው ገድለውታል። ክስተቱ በመላ ሀገሪቱ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሶ ነበር።
ጥቃቱን የፈጸሙት ሰዎች በወቅቱ ራሳቸውን ፎቶ ያነሱ እና ቪዲዮ የቀረጹ ሲሆን፤ በኋላ ለመደበቅ ቢሞክሩም ፣ ጉዳዩ ያሳሰባቸውና ፍትህን የሚሹ ዜጎች ፎቶግራፎቹን ሰብስበው በማስቀመጣቸው፣ በቀላሉ ሊለዩ እና ለፍርድ ሊቀርቡ ችለዋል።
አልጄሪያ ከሰላሳ ዓመታት በፊት የሞት ቅጣት እንዲቀር በማድረጓ፣ በግለሰቦቹ ላይ የተላለፈው የሞት ቅጣት ወደ ዕድሜ ልክ እስራት ይቀየራል ተብሏል።
ክስ ከተመሠረተባቸው 94 ግለሰቦች ውስጥ 27 የሚሆኑት ጥፋተኛ አለመሆናቸው ሲነገር፣ 29 የሚሆኑት ደግሞ ከ 3 እስከ 20 ዓመታት እስር ተፈርዶባቸዋል።
መድረክ / ፎረም