በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዓለምዋጭ የስደተኞች መጠለያ አንድ ታጋች በታጣቂዎች መገደሉ ተገለጸ


በሰሜን ጎንደር ዞን በዳባት ወረዳ በሚገኘው የዓለምዋጭ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ፣ ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ፣ አንድ ኤርትራዊ በታጣቂዎች መገደሉን ስደተኞች ተናገሩ።

በታጣቂዎች ተገደለ የተባለው ስደተኛ፣ ባለፈው ሳምንት ኀሙስ፣ ግንቦት 8 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ ከሌሊቱ 5 ሰዓት ተኩል፣ ከመጠለያ ጣቢያ ታግቶ መወሰዱንና ቅዳሜ ዕለት ደግሞ በጫካ ውስጥ ተገድሎ መገኘቱን፣ ስደተኞቹ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

የመጠለያ ጣቢያው የሚገኝበት የዳባት ወረዳ የጭላ ቀበሌ አስተዳደር ደግሞ፣ ግድያው መፈጸሙን አረጋግጦ፣ ጉዳዩን ፖሊስ እየተከታተለው ነው፤ ብሏል፡፡

ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን አንድ ስደተኛ በሰጡት አስተያየት፣ ግለሰቡ ታግቶ ከተወሰደ በኋላ፣ ታጣቂዎቹ የማስለቀቂያ ገንዘብ በስልክ ይጠይቃሉ በሚል በመጠባበቅ ላይ ሳሉ መገደሉን መስማታቸውን ተናግረዋል።

የዓለምዋጭ መጠለያ ጣቢያ የሚገኝበት የጭላ ቀበሌ አስተዳዳሪ አቶ ምናለ ግብነህ፣ የግለሰቡን መገደል ለአሜሪካ ድምፅ አረጋግጠው፣ ጉዳዩን ፖሊስ እያጣራው እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

በመጠለያ ጣቢያው፣ እንዲህ ዓይነት ኹኔታ በተደጋጋሚ እንደሚያጋጥምና ሰዎችም እንደሚገደሉ የተናገሩት የመጀመሪያው አስተያየት ሰጪ፣ የዚኽ ግለሰብ አሟሟት ግን እንደተለየባቸው ገልጸዋል፡፡ የአካባቢው የጸጥታ ኹኔታ አስጊ በመኾኑ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡትም ጠይቀዋል፡፡

አስተያየት የሰጡን ሌላው የመጠለያ ጣቢያው ነዋሪም፣ የግለሰቡ በዚኽ መልኩ መገደል፣ እኛ ስደተኞች በአስጊ ኹኔታ ውስጥ እንዳለን ያሳያል፤ ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ጥበቃ እንዲያደርግላቸውም ተማፅነዋል፡፡

ስለ ጉዳዩ፣ ከኢትዮጵያ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት፣ ከሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳደር እና ከዞኑ የጸጥታ ጽሕፈት ቤት ምላሽ እና አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡

በዓለምዋጭ መጠለያ ጣቢያ አካባቢ ስላለው የጸጥታ ችግር፣ ነዋሪዎች ከዚኽም ቀደም ተደጋጋሚ አቤቱታ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ ከአንድ ወር በፊት፣ ከመጠለያ ጣቢያው ታጣቂዎች አንድ ኤርትራዊ ሕፃንን አግተው በመውሰድ፣ 400ሺሕ ብር የማስለቀቂያ ቤዛ እንደጠየቁና ከቀናት በኋላ ግን በ200ሺሕ ብር ክፍያ እንደለቀቁት መዘገባችን ይታወሳል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG