የአል-ሻባብ ታጣቂዎች አንድ በሞቃዲሾ የሚገኝ ሆቴልን ትላንት ማምሻውን አግተው ከያዙ በኋላ ማስለቀቁን የሶማሊያ ፖሊስ አስታውቋል።
በከፍተኛ ጥበቃ ሥር የነበረውን ሆቴል አግተው የነበሩት የአል-ሻባብ ታጣቂዎች በሙሉ መገደላቸውንና ሁኔታዎች በቁጥጥር ሥር መሆናቸውን የፖሊስ አዛዦች ለኤፍፒ ዜና ወኪል ተናግረዋል። የፀጥታ ኃይሎችም አካባቢውን ፈትሸው ከስጋት ነፃ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ለአንድ ሰዓት ያህል በዘለቀው እገታ ሦስት ሰዎች ሲገደሉ 27 ሰዎች መቁሰላቸውን ፖሊስ ዛሬ ዓርብ አስታውቋል። የፀጥታ ኃይሎች አምስት ታጣቂዎችን መግደላቸውም ታውቋል።
ታጣቂዎቹ ማገታቸውን ተከትሎ፣ የፀጥታ ኃይሎች ኤስ ዋይ ኤል የተሰኘውን ሆቴል እንደከበቡ፣ በኋላም ፍንዳታ መሰማቱን እንዲሁም ከውስጥ ተኩስ መከፈቱን ባለሥልጣናትና የዓይን እማኞች ተናግረዋል።
አል-ሻባብ ለጥቃቱ ኃላፊነት ወስዷል። ሆቴሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ሕግ አውጪዎች የሚያዘወትሩት እንደሆነም ታውቋል። አል-ሻባብ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ በሆቴሉ ላይ ጥቃት ሠንዝሯል።
መድረክ / ፎረም