በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአፋር ውጊያ ሰብዓዊ አገልግሎት እንደተስተጓጎለ ተመድ ገለጸ


ፎቶ ፋይል፦ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች
ፎቶ ፋይል፦ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫቸው በኢትዮጵያ አፋጣኝ የሰብዓዊ ጉዳይ ዙሪያ በሰጡት መረጃ በአፋር ያለው ውጊያ የረድኤት አቅርቦቱን አሁንም እንዳስተጓጎለ ነው ብለዋል።

በረድኤት ሥራው የተሰማሩትን የመንግሥታቱ ድርጅት ሰራተኞች ዋቢ አድርገው በሰጡት አስተያየት፣ የአፋሩ ውጊያ ምግብ እና ሌሎች የዕርዳታ ቁሳቁሶች የሚያስፈልጋቸው ከአምስት ሚልዮን በላይ ተረጂዎች ወዳሉበት አጎራባቹ የትግራይ ክልል ይላክ የነበረውን ዕርዳታ እንዳይደርስ አድርጓል ነው ያሉት። ግጭቱ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ እንዲፈናቀልም ምክኒያት መሆኑን አመላክተዋል።

በነዳጅ እና የጥሬ ገንዘብ፣ እንዲሁም የረድኤት አቅርቦት እጥረቱ የሰብዓዊ እርዳታ ሥራውን በእጅጉ መቀነሱን የተናገሩት ቃል አቀባዩ፣ ባለፈው ሳምንት አንድ ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅት ከ14 ሜትሪክ ቶን በላይ መድሃኒት ወደ ትግራይ ማስገባት መቻሉን ተናግረዋል። ይሁንና የነፍስ አድን ዕርዳታውን በአየር ማድረስ መቻሉ መልካም ቢሆንም መጠኑ ከሚያስፈልገው አንጻር ግን በእጅጉ ያነሰ ነው ነው ያሉት።

ዱጃሪች አክለውም ቁጥራቸው ስድስት መቶ ሺህ የሚጠጋ ሕጻናትን መድረስ የቻለ የሁለተኛ ዙር የጸረ-ኩፍኝ ክትባት ዘመቻ በትግራይ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

በነዳጅ እጥረት ሳቢያ የጤና ባለሙያዎች በአንዳንድ አካባቢዎች የክትባት አገልግሎት ለመስጠት እስከ 35 ኪሎ ሜትር በእግር ለመጓዝ መገደዳቸውን ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ በትግራይ የተወሰነ የምግብ ሥርጭት መቀጠሉን ተናግረው ካለፈው የጥቅምት ወር አጋማሽ አንስቶ ለ880 ሺህ ሰዎች ምግብ መታደሉን፤ ይህም መጠን በየሳምንቱ መድረስ የነበረበት ነው ብለዋል።

በአፋር የቀጠለው ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ከቀያቸው ማፈናቀሉን ገልጠው ተረጂዎቹ አስቸኳይ ምግብ እና የጤና አገልግሎት ዕርዳታ ማግኘት አለባቸው” ብለዋል። ሆኖም ባለው የጸጥታ ችግር ሳቢያ ወደ አካባቢው ለመድረስ ያላቸው ዕድል ግን የተገደበ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ቀደም ሲል ሊደርሱ በቻሉባቸው ከፊል የአፋር ክልል አካባቢዎች ባለፈው ሳምንት 85 ሺህ ያህል ሰዎች የምግብ እርዳታ ማግኘታቸውን ከጥቅምት ወር አጋማሽ አንስቶም የምግብ ዕርዳታ ማግኘት የቻሉት ሰዎች ቁጥር በጠቅላላው 500 ሺህ መድረሱን አስረድተዋል።

ዱጃሪች በመግለጫቸው አክለውም በጎረቤት አማራ ክልል ቁጥሩ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆን ሰው ባለፈው ሳምንት መርዳት ተችሏል ብለዋል።

XS
SM
MD
LG