ዋሺንግተን ዲሲ - አዲስ አበባ —
የምሥራቅ ናይል ተፋሰስ አካል በሆኑት በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል የአባይ አጠቃቀምና የታላቁ ኅዳሴ ግድብ የመርኅ ስምምነት ዛሬ ተፈርሟል፡፡
ስምምነቱ የተፈረመው በሦስቱ ሃገሮች መሪዎች፤ በሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሃሰን አል-በሺር፣ በግብፁ ፕሬዚዳንት አብደልፋታህ ኤል-ሲሲና በኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ ኻርቱም ላይ በሱዳኑ ሪፐብሊካን ቤተመንግሥት ውስጥ በተከናወነ ሥነ-ሥርዓት ነው፡፡
የሰነዱን ይዘትና የስምምነቱን ምንነት አስመልክቶ የኢትዮጵያን የውኃ፣ ኢነርጂና የመስኖ ሚኒስትር አቶ አለማየሁ ተገኑ ለቪኦኤ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ሚኒስትሩ በዚሁ ለቪኦኤ በሰጡት መግለጫቸው ላይ የአባይ አጠቃቀም በፍትሐዊነት ላይ ተመሥርቶ በሦስቱም ሃገሮች ላይ ብዙ ጉዳት የማያስከትል፤ በትብብር መርኅ ላይ የተመረኮዘ እንዲሆን የመርኅ ስምምነት ላይ መደረሱን እና አባይ ለሦስቱም ሃገሮች ሕዝቦች እኩል የሕይወትና የልማት ምንጭ መሆኑ በሠነዱ ላይ መስፈሩን አመልክተዋል፡፡
ከአቶ አለማየሁ ተገኑ ጋር የደረገውን ቃለምልልስ ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡