በትናንትናው ዕለት ቶሮንቶ ውስጥ አውሮፕላኑ ከተከሰከሰ በኋላ ወደ አካባቢው ሆስፒታሎች ከተወሰዱ 21 መንገደኞች ውስጥ 19ኙ ታክመው መውጣታቸውን ዴልታ አየር መንገድ ዛሬ ማክሰኞ አስታወቀ። ባለሥልጣናት በቀጠናው በረራ በመብረር ላይ የነበረው ጄት በማረፍ ሂደት ለምን እንደተገለበጠ ለማወቅ ምርመራ ቀጥለዋል።
የካናዳ የትራንስፖርት ደኅንነት ቦርድ መርማሪዎች በዴልታ አየር መንገድ ኢንዴቨር ኤር ቅርንጫፍ የሚተዳደረው ሲ አር ጄ 900 አውሮፕላን በቶሮንቶ ፒርሰን አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ እንዴት በጀርባው ሊወድቅ እንደቻለ ለማወቅ የሚደረገውን ምርመራውን እየመሩ ነው።
ከሚኒሶታ ሴንት ፖል አውሮፕላን ማረፊያ በተነሳው ዲኤል 4819 አውሮፕላን ላይ ምን እንደተከሰተ እስካሁን ግልጽ አልሆነም ።የአውሮፕላን አደጋዎቸ በተለያዩ ምክንያቶች ይከሰታሉ።
90 ሰዎችን ማሳፈር የሚችለው አውሮፕላን በካናዳው ቦምባርዲየር ኩባንያ የተሠራ ሲኾን የጄኔራል ኤሌክትሮኒክስ ኩባንያ ያመረተውን ሞተር ይጠቀማል። አደጋው ከተከሰተ በኋላ የተቀረጹ ምስሎች ከክንፎቹ መካከል ቢያንስ አንደኛው መገንጠሉን ያሳያሉ።
የቶሮንቶ ፒርሰን አውሮፕላን ማረፊያ፣ በትናንትናው ዕለት ቀደም ብሎ በስፍራው በጣለው እና ከ22 ሴ.ሜ በላይ ጥልቅት ባለው በረዶ ምክንያት የታጠፉ በረራዎችን ለማስተካከል እየጣረ እንደነበረ አስታውቋል።
በአደጋው ወቅት ኃይለኛ በረዶ የቀላቀለ ነፋስ እንደነበረ የበረራ ክትትል ድረ ገጽ የሆነው ፍላይት ራዳር 24 አስታውቋል።
መድረክ / ፎረም