በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያና ሶማሊያ የደረሱበትን ሥምምነት “ካለ ምንም መዘግየት” ተግባራዊ እንዲያደርጉ የአፍሪካ ኅብረት ጠየቀ


የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ

ኢትዮጵያና ሶማሊያ በመካከላቸው ተፈጥሮ የነበረውን ውጥረት መፍትሄ ለመስጠት የደረሱበትን ሥምምነት “ካለ ምንም መዘግየት” ተግባራዊ እንዲያደርጉ የአፍሪካ ኅብረት ጠየቀ።

የሁለቱ ሃገራት መሪዎች “ጠቃሚ የሆነ ርምጃ” ወስደዋል፣ ያሉት የኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት፣ ሆኖም ግን “የተስማሙባቸውን ጉዳዮች ካለመዘግየት ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው” ሲሉ በX ማኅበራዊ መድረክ ላይ ባሰፈሩት መልዕክት አስታውቀዋል።

የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ዋና ፀኅፊ ወርቅነህ ገበየሁ በበኩላቸው፣ “አስፈላጊ እርምጃ” ብለው የገለጹት ሥምምነት፣ “የሁለትዮሽ ጉዳዮችን በወዳጅነት መንፈስ መፍታትን ያሳየ ነው” ብለዋል።

ኢትዮጵያ የሶማሊላንድን የባሕር ዳርቻ በኪራይ ለመያዝ ከአንድ ዓመት በፊት ሥምምነት መፈጸሟን ተከትሎ፣ ሉዐላዊነቷ እንደተደፈረ የምትገልጸው ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋራ ውጥረት ውስጥ ከርማለች፡፡ ሶማሊላንድ ለፈጸመችው ሥምምነት በአጸፋው ከኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊና ይፋዊ ዕውቅና እንደምታገኝ ብትገልጽም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህ እንደሚሆን ፈጽሞ አረጋግጦ አያውቅም።

የሶማሊያ እና የኢትዮጵያ መሪዎች ትላንት ረቡዕ ቱርክ ላይ ሰዓታት የፈጀ ውይይት ካደረጉ በኋላ፣ “ታሪካዊ” ስትል የገለጸችው ሥምምነት በሁለቱ ሃገራት መካከል መፈረሙን አንካራ አስታውቃለች፡፡

የሥምምነቱ ዝርዝሮች በይፋ ባይገለጹም፣ ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉዐላዊነት ባከበረ መልኩ የባሕር በር እንደምታገኝ ተመልክቷል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG