በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

መሪዎች ፈረንሳይ ለአፍሪካ ያቀረበቸውን ጥሪ ደገፉ


የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ማርኮን የአይ ኤም ኤፍ ድሬክተር ክሪስታሊና የሴናጋል ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል እና የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት እና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ፌሊክስ ሼስኬዲ
የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ማርኮን የአይ ኤም ኤፍ ድሬክተር ክሪስታሊና የሴናጋል ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል እና የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት እና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ፌሊክስ ሼስኬዲ

በኮቪድ 19 የተጠቁትን የአፍሪካ አገሮች ለመርዳት በፓሪስ የተካሄደው ስብሰባ ትናንት ማክሰኞ ለአፍሪካ ከፍተኛ የገንዘብ እርዳታና ክትባት እንዲደረግ፣ እንዲሁም በአፍሪካና ለጋሽ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት መጠነ ሰፊ ወደሆነ ግንኙነት እንዲሸጋገር ጥሪ በማቅረብ ተጠናቋል፡፡

የስብሰባው አዘጋጅ አገር፣ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማርኮን፣ ለአፍሪካ አገሮች አዳዲስ እርዳታዎች እንዲደረጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የፓሪስ ስብሰባ ዋና ዓላማም ነገሮች ወደዚያው እንዲያመሩ ለማሳሰብ መሆኑን ተነግሮለታል፡፡

ፕሬዝዳንት ማርኮንም ሆኑ ሌሎቹ መሪዎች ካወጡት እቅድ መካከል በኮቭካስ የክትባት ስርጭት መርሃ ግብር መሠረት፥ በ2021 መጨረሻ ላይ ለአፍሪካ የሚሰጠው የኮቪድ 19 ክትባት፣ በእጥፍ እንዲጨምር የሚለው ይገኝበታል፡፡

መሪዎች ፈረንሳይ ለአፍሪካ ያቀረበቸውን ጥሪ ደገፉ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:27 0:00

እንዲሁም የዓለም የፋይናንስ ድርጅት አይ ኤም ኤፍ አባል አገራት፣ ለአፍሪካ አገሮች የሚያስቀምጡትን መጠባበቂያ፣ በሶስት እጥፍ አሳድገው ወደ 100ቢሊዮን ዶላር እንዲያደርሱና፣ አፍሪካም የኮቪድ 19 ክትባቶችን ማምረትና ማሰራጨት እንትድትችል እገዛ መስጠት የመሳሰሉትን ተካተውበታል፡፡

ፕሬዚዳንት ማክሮን፣ “ይህ ያለንበት ወቅት ስፋት እና ዘላቂነት ባለው መንገድ፣ እስከዛሬ ላልተፈቱ ችግሮች ምላሽ የምንሰጥበት ወቅት ነው” ብለዋል፡፡

ለአፍሪካ የኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን ዘላቂ የሆኑ አዳዲስ ስምምነቶች በአንድ ምሽት የሚገኙ ባይሆኑም ውይይቱ አዳዲስ ሀሳቦች እንዲመነጩ ያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ከሴኔጋል ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል የተደመጠውም መልዕክት ተመሳሳይ ነው፡፡ አፍሪካ ከበለጸጉ አገሮች ጋር በምታደርገው ግንኙነት መልኮች እየተለወጡ ነው፡፡ ብለዋል፡፡

“ፕሮግራሞችን በግዴታ እንዲፈጸሙ ግፊት ከማድረግ ይልቅ አስፈላጊ በሆኑ ፕሮጀክቶች ላይ ወደ መነጋገር እየተቀየረ ነው፣ ምክንያቱም ችግራችንን ከማንም በላይ የምናውቀው እኛ ነንና” ብለዋል ፕሬዚዳንት ማኪ፡፡

ከአንድ ዓመት በላይ የፈጀው የሰብሰባው ዝግጅት፣ የተለያዩ አገራት መሪዎችን፣ ከአፍሪካ፣ ከአውሮፓና፣ ከዓለም አቀፉ የፋይናንስ ተቋማት ያሰባሰበ ሲሆን፣ በኮቪድ 19 ሳቢያ የተፈለገው ያህል ባይሆንም፣ ስለ አፍሪካ በቀረቡት የተለያዩ የመረጃ ቋቶች ላይ የተደገፈ ስብሰባ እንደነበር ተመልክቷል፡፡

ምንም እንኳ አፍሪካ፣ ከሌላው የዓለም ክፍል፣ በወረርሽኙ የደረሰባት ጉዳት አነስተኛ ነው እንኳ ተብሎ ቢታሰብ፣ በቱሪዝም እና ሌሎች የገቢ ምንጮቿ ግን የደረቁባት መሆኑ ተመልክቷል፡፡

የአፍሪካ ኢኮኖሚ በዚህ ዓመት ያድጋል ተብሎ የሚታሰበው ከ3 ከመቶ ጥቂት ያለፈ ነው፡፡ ይህ ከአማካዩ የዓለም የኢኮኖሚ እድገት ግማሽ ያህል ያነሰ ነው፡፡ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ወደ 300 ቢሊዮን ዶላር ያህል የወጭ እጥረት እንደሚገጥመውም ተመልክቷል፡፡

ይህ በመሆኑም ባለሙያዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተጫማሪ አፍሪካውያን ወደ ድህነቱ ጎራ ይቀላቀላሉ የሚል ግምት አላቸው፡፡ የኮቪድ 19 ክትባትንም በሚመለከት እሳክሁን ክትባቱን ያገኙት አፍሪካውን ቁጥር ከ3 ከመቶ ያነሰ መሆኑ ተነግሯል፡፡

አፍሪካ ከገጠማት የጤና ቀውስ ሳታወጣ ከኢኮኖሚው ቀውስ የምትወጣበት ዘላቂ መንገድ አለ ተብሎ ጨርሶ አይታመንም ያሉት ደግሞ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት IMF ኃላፊ ክሪስታሊና ጂኦርጄቫ ናቸው፡፡

ኃላፊዋ አያይዘውም “የክትባቱን ዘመቻ ማሳደግ ብዙ ትሪሊዮን ዶላሮችን የሚያስገኘው ለአፍሪካውያን ብቻ ሳይሆን ለበለጸጉ አገሮችም ጭምር ነው” ይላሉ፡፡ አስፈላጊነቱም ሲገልጹ

“ከዚህ የጤና ቀውስ በአስቸኳይ የምንወጣበትን መንገድ ሠርተንበታል፡፡ ከመጨረሻው እልባት ለመድረስም በ2021 መጨረሻ፣ በየትኛውም የዓለም ክፍል ለሚገኝ ማንኛውም ሰው 40 ከመቶ የሚሆነውን ክትባት መስጠት አለብን፡፡ በ2022 አጋማሽም ደግሞ እንዲሁ 60 ከመቶ የሚሆነውን ማስከተብ ይኖርብናል፡፡ ይህ ለአፍሪካ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡” ብለዋል፡፡

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት እና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ፌሊክስ ሼስኬዲ አፍሪካ የክትባቱን ማምረትና ስርጭት ላይ እንድት ሳተፍ ቢደረግ ይጠቅማል ይላሉ፡፡

“ከውጭ ዓለም ተሰርቶ የመጣውን ክትባት ለመውሰድ የሚያመነቱ አንዳንድ ወገኖችን ስጋት ሊያስወግድ ይችላል፡፡”

ሊቀመንበሩ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አፍሪካ ሽብርተኞችን ለመዋጋት የምታደርገውን ጥረት ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ለአፍሪካ ተጨማሪ የእዳ ቅነሳ እንዲደረግና፣ ለአህገሪቱ የገባያ እድሎች እንዲከፈቱም ጠይቀዋል፡፡

በሌላም የአፍሪካም መሪዎች መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የበኩላቸውን ጥረት ማድረግ፣ ሙስናን መዋጋትና የአፍሪካ ወጣቶችን መደገፍ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በፋይናንስ ጉዳዮች ላይ ያተኮረው ስብሰባ ትናንት ማክሰኞ የተጠናቀቀ ሲሆን የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የIMF አባል አገራት ሱዳን ያለባትን በቢሊዮኖች የሚቆጠር እዳ እንዲሰረዝ ተስማምተዋል፡፡

“ካርቱም የምታደርገውን የዴሞክራሲ ሽግግር ለማገዝ” በሚል፣ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮም ሱዳን ለአገራቸው መክፈል የነበረባትን የ5 ቢሊዮን ዶላር እዳ የተሰረዘላት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የሰማችሁት ሊሳ ብራያንት ከፓሪስ የላከቸውን ዘገባ ነበር፣ ለአሜሪካ ድምጽ ደረጀ ደስታ ነኝ ጤና ይስጥልኝ፡፡

የቪኦኤ ዘጋቢ ሊሳ ብራያንት ከፓሪስ ከላከቸው ዘገባ የተወሰደ፡፡

XS
SM
MD
LG