በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አፍሪካ በጋዜጦች በኢትዮጵያ የተከሰተው ኤል-ኒኖ እና የአፍሪካ ህብረት ፓስፖርት ይዳስሳል


ኢትዮጵያ ምንም አይነት አስተዋጽኦ ባላደረገችበት የኤል-ኒኖ ድርቅ መሰቃየትዋ እንደሚያስዝናቸው የቀድሞዋ የአየርላንድ ፕረዚዳንት ገለጹ፣ የአፍሪቃ ህብረት ለመላ የአፍሪቃ ዜጎች አንድ ፓስፖርት ለማውጣት ማቀዱ ታወቀ፣ ተቆርቋሪ አፍሪቃውያን የአፍሪቃ ህብረት አባል ሀገሮች ከአለም አቀፍ የወንጀል ፍርድቤት አባልነት እንዳይወጡ ዘመቻ ጀመሩ የሚሉትን ርእሶች ይዳስሳል።

የቀድሞዋ የአየርላንድ ፕረዚዳንት ሜሪ ሮቢንሰን 10 ሚልዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የአየር ለውጥ ባስከተለው ቀውስ ምክንያት ባለፉት 50 አመታት ውስጥ ባልታየ አይነት ድርቅ መሰቃየታቸው ተገቢ አይደለም ማለታቸውን ቤልፋስት ቴሌግራፍ የተባለው ድረ-ገጽ ጠቅሷል።

የቀድሞዋ የአየርላንድ ፕረዚዳንት ሜሪ ሮቢንሰን
የቀድሞዋ የአየርላንድ ፕረዚዳንት ሜሪ ሮቢንሰን

በአሁኑ ወቅት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ለውጥና ኤል ኒኖ የሚያስከትለው የአየር ጠባይን አስመልክቶ ልዩ የድርጅቱ ልእክት የሆኑት የቀድሞ የድርጅቱ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ኮሚሽነር ሜሪ ሮቢንሰን ኢትዮጵያ ራስዋ አስተዋጾ ባላደረገችበት የአየር ለውጥ ምክንያት መሰቃየትዋ ያሳዝነኛል ማለታቸውን ድረ-ገጹ ጠቁሟል።

ኣይሪሽታይምስ የተባለው የአየርላንድ ድረ-ገጽ ደግሞ ሜሪ ሮቢንሰን በያዝነው ሳምንት ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት በሀገሪቱ የተከሰተውን የድርቅ ሁኔታ ለማቃለል በተደረገው ጥረት የ $518 ሚልዮን ዶላር የረድኤት ክፍተት አለ ማለታቸውን ገልጿል። የአለም ማህበረሰብ በአሁኑ ወቅት በስደተኞች መጉረፍ፣ በብሪታንያ ከአውሮፓ ህብረት መውጣትና ግጭት በሚካሄድባቸው አከባቢዎች ላይ በመጠመዱ የድርቁ ጉዳይ አለም አቀፍ ትኩረት ለማግኘት አልቻለም ሲሉም አስገንዝበዋል።

ሜሪ ሮቢንሰን ከኢትዮጵያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴድሮስ አድሃኖም ጋር ተገናኝተው ከተናጋገሩ በኋላ ድርቁ ያጠቃው ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ደቡባዊ አፍሪቃም ክፉኛ ጎድቷል። ሆንድራስን የመሳሰሉት የማዕከላዊ አሜሪካ ሀገሮች፣ ቬትናምን የመሳሰሉት የእስያ ክፍሎችም ኤል ኒኖ ባስከተለው ድርቅ እንደተጎዱ ገልጸዋል።

የቀድሞዋ የአየርላንድ ፕረዚዳንት ሜሪ ሮቢንሰን ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
የቀድሞዋ የአየርላንድ ፕረዚዳንት ሜሪ ሮቢንሰን ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

ሲኤንኤን የተባለው የዜና ስርጭት መረብ ድረ-ገጽ ደግሞ የአፍሪቃ ህብረት በመላ 54 የአፍሪቃ አባል ሀገሮች ሊያገለግል የሚችል ፓስፖርት ለማውጣት ማቀዱን ዘግቧል። የአውሮፓ ህብረት በብሪታንያ መውጣት ምክንያት በተናጋበት በአሁኑ ወቅት የአፍሪቃ ህብረት የጋራ የሆነ ፓስፖርት በማውጣት በበለጠ ለመቀራረብ እየጣረ ነው ይላል የሲኤንኤን ዘገባ።

የኤለክትሮኒክ ፓስፖርቱ በመጪው እሁድ በርዋንዳ መዲና ኪጋሊ በሚካሄደው የህብረቱ ጉባኤ ይፋ ተደርጎ ለርእሳነ-ብሄራትና ለከፍተኛ ባለስልጣኖች ይሰጣል። የአፍሪቃ ህብረት እአአ እስከ 2018 ዓም ባለው ጊዜ ውስጥ በሁለት አመታት ውስጥ ማለት ነው ፓስፖርቱን ለመላ የአፍሪቃ ዜጎች ለመስጠት ማቀዱን ዘገባው ጨምሮ ገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኒውስ24 የተባለው መሰረቱ ደቡብ አፍሪካ የሆነው ድረ-ገጽ በበኩሉ በአፍሪቃ ማዕዝናት ያሉት ተቆርቋሪዎች የአፍሪቃ ህብረት አባል ሀገሮች ከአለም አቀፍ የወንጀል ችሎት ለመውጣት ያላቸውን ሃሳብ እንዲቀለብሱ ጫና የማድረግ ዘመቻ መጀመራቸው ዘግቧል።

ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያድምጡ።

አፍሪካ በጋዜጦች ኢትዮጵያ የተከሰተው ኤል-ኒኖ እና የአፍሪካ ህብረት ፓስፖርት ይዳስሳል
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:19 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

XS
SM
MD
LG