በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኦሮሚያ የሚካሄደው እንቅስቃሴ እና ሌሎች ርእሶች በአፍሪቃ በጋዜጦች ዝግጅት


የብሔራዊ ምርጫ አዲስ አበባ ውስጥ በሚካሄድበት ግዜ ኢትዮጵያውያን ጋዜጣ እያነበቡ እአአ 2015 ዓ.ም. [ፎቶ ፋይል - ሮይተርስ]
የብሔራዊ ምርጫ አዲስ አበባ ውስጥ በሚካሄድበት ግዜ ኢትዮጵያውያን ጋዜጣ እያነበቡ እአአ 2015 ዓ.ም. [ፎቶ ፋይል - ሮይተርስ]

በኦሮሚያ የሚካሄደው እንቅስቃሴ፣ ኤል ኒኖ የአፍሪቃን የኢኮኖሚ ሞተር ማቀዝቀዙ ተዘገበ፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ደቡብ አፍሪቃውያን ፕረዚዳንት ጃኮብ ዙማ ከስልጣን እንዲወርዱ ጠየቁ የሚሉትን ርእሶች ነው በዛሬው ቅንብራችን የምንመለከተው።

የኒው ዮርክ ታይምስ (New York Times) ጋዜጣ ድረ-ገጽ ላይ የወጣ ዘገባ በኦሮሚያ ስለሚካሄደው ተቃውሞ ሲዘግብ ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ በሚገኘው ቡራዮ ከተማ ውጥረት እንደሰፈነ ይገልጻል። አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ፌደራል ፖሊሶች አከባቢውን እንደሚጠብቁና በቅርቡ አንድ አውቶብስ በእሳት የጋየበት ምልክት እንደሚታይ ጠቁሟል።

በኦሮሚያ ከተማዎች ካለፈው ወር አንስቶ ሃይል ተጠቃሚነት የተቀላቀለባቸው ተቃውሞዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን ዘገባው ጠቅሷል። የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ ሊቀ-መንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ካለፉት ጥቂት ሳምንታት ወዲህ ከጸጥታ ሃይሎች ጋር በተካሂደው ግጭት ቢያንስ 50 ሰዎች እንደተገድሉ ይገመታል ብለዋል። መንግስት ግን አምስት እንደሞቱ ነው የሚናገረው።

ፕሮፌሰር መራራ አንዳንድ ተቃዋሚዎች በግጭት ተግባር እንደተሳተፉ አምነው ተቀብለዋል። ሆኖም መንግስት እንቅስቃሴው ተአማኒነት እንዳይኖረው ሲል ችግሩን አባብሷል ብለዋል።

አዲስ አበባ በሚገኘው የጸጥታ ጉዳይ ጥናት ማዕከል ምርምር የሚያካሄዱት ሀሌሉያ ሉሌ መንግስት ስለ ማስተር ፕላኑን ህዝንቡን ከማስረዳት አንጻር በቂ ስራ እንዳልሰራ አምኖ ተቀብሏል ብለዋል። “ይሁንና ተቃውሞው ከማስተር ፕላን የዘለለ እንደሆነ ዘገባው ሲጠቅስ የፈደራሊስም ተገቢ አተገባብበርን፣ አዲስ አበባ ከሚያካብብዋት የኦሮሞ ማህበረሰብ ጋር ያላት ግንኙነትንም እንደሚመለከት፤ የአስተዳደር ጉድለትንና የሰብአዊ መብት አለመከበር ጉዳይንም እንደሚያነሱ ሀሌሉያ ሉሌ ማስገንዘባቸውን፤ ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ላይ የወጣው ጽሁፍ አስነብቧል።

የብሉምበርግ የዜና አገልግሎት በበኩሉ በኦሮሚያ ሰለሚካሄደው ተቃውሞ በዘገበበት ጽሁፍ በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ላይ የተጀመረው ተቃውሞ ባለፈው ቅዳሜ አመያ ወረዳ ላይ በኦሮሞዎችና በአማሮች መካከል ግጭት አስክትሏል ሲሉ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ካውንስል ዋና ስራ አስኪያጅ ብጻተ ተረፈ (Betsate Terefe) መናገራቸውን ጠቅሷል።

ኢትዮጵያ ያለው የኔዘርላንድስ ኤምባሲ ሁለት የዳች የእርሻ ቦታዎች በእሳት እንደጋዩ በምዕራብ ሸዋ ቀጠናም አንድ ሌላ የእርሻ ቦታ እንደተቃጠለ በኢመይል እነደገለጸ የብሉምበርግ የዜና አገልግሎት ጠቅሷል። ባለፈው አርብ ደግሞ ስላግሮው ግራዝላንድ አግሮ ኢንዱስትሪ (Solagrow Grazeland Farm Agro Industry) እንደወደሙ። የሊንሰ (Linssen) የጽጌረዳ ተክልም በዲንጋይ እንደተደበደበ ብሉምበርግ የዜና አገልግሎት አውስቷል።

ኤል ኒኞ (El Nino) የተባለው የአየር ለውጥ መከሰት የአፍሪቃን የኢኮኖሚ እድገት ሞተርን እያቀዘቀዘ ነው በሚል ርእስ ዋል ስትሪት ጆርናል ጽረ-ገጽ ላይ የወጣው ጽሁፍ በበኩሉ የውቅያኖስ ውሀ እየሞቀ መሄድ ባስከተለው ደረቅ አየር ምክንያት የተከሰተ ድርቅ በሚልዮኖች በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ የረሀብ ሁኔታ ደቅኗል። በአህጉሪቱ የሚካሄደውን አህጉር አቀፍ የንግድ ልውውጥንም እያሰናከለ ነው ይላል።

በአህጉሪቱ በተከሰተው ከባድ ድርቅ የእህል ማጎር በማስከትሉ ከ 30 ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ወደ ረሀብ እያመራ እንደሆነ ይገልጻል።

ኤል ኒኞ (El Nino) የተባለውን የአየር ለውጥ ያስከተለው ድርቅ በሰላሳ አመተት ውስጥ ያልተየ አይነት ከባድ ድርቅ በማድረሱ በብዙ የአፍሪቃ ሀገራት ለሁለተኛ ጊዜ በቂ መኸር አልተገኘም። የኤል ኒኞ (El Nino)መቅሰፍት ያባባሰው የአፍሪቃን ድርቅ ብቻ ሳይሆን በኢንዲኒዥያና በአከባቢዋ በያዝነው ወር የሰደደ እሳት ለቋል።

በኤል ኒኖ ምክንያት የሚከሰተው ድርቅና የጎርፍ መጥለቅለቅ ምን ያህል እንደሚባባስ በያዝነው ወር ፓሪስ በተካሂደው የአየር ለውጥ ጉባኤ ላይ የሀገሮች መሪዎች ተወያይተውበታል።

ባለፈው ቅዳሜም የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ፣ የአለም የአየር ሙቀት በአማካኝ ከሁለት ዲግሪ ሰልሸስ በላይ እንዳይጨምር ለማድረግ ተስማምተዋል። ታዳጊ ሀግሮች ስምምነቱን በተግባር ላይ ለማዋል እንዲችሉም በአመት ከ $100 ቢልዮን ዶላር በላይ ለማቅረብ ወስነዋል ይላል።

የወቅቱ የድርቅ ሁኔታ የአፍሪቃን በኢኮኖሚ እድገት መገስገስን ወደ ኋላ መልሷል። የአፍሪቃ ዋናዋ የንግድ አጋር የሆነችው ቻይና ኢኮኖሚ እየቀዘቀዘ መሄድ ጋር ተዳምሮ እድገቱ በአለም ደረጃ የገንዘብ ቀውስ ደርሶ ከነበረበት ጊዜ ወዲህ ባልታየ ሁኔታ ዝቅ እንዲል ማደርጉን ዎል ስትሪት ጆርናል ላይ የወጣው ጽሁፍ ጠቁሟል።

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በያዘነው አመት የከፋ ድርቅ እንደተከሰተ ጽሁፍ ሲገልጽ በሳባት አመታት ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ ከዩናትድ ስቴትስ (United States)ና የተትረፈረፈ ምርቷን ይሸምቱ ከነበሩት ዚምባባዌንና ስዋዚላንድን ከመሳሰሉት ሃገሮች ቦቆሎ ማስገባት መጀመርዋን ዘገባው አውስቷል።

ዚምባብዌና ታንዜንያ የእህል ምርት ከአገር እንዳይወጣ ማገዳቸውን፣ ዛምቢያም የነሱን ፈለግ ለመከተል ማቀድዋን፣ እንዲህ አይነቱን ገደብ ደግሞ ከአለም እጅግ ደሀ የሚባሉትን ማላዊንና ደቡብ ሱዳንን የመሳሰሉትን ሀገሮች እንደሚጎዳ ጽሁፍ ጠቁሟል።

ኢኮኖሚዋ በፍጥነት እያደገ ያለውና የአውሮፓና የቻይና መዋዕለ-ነዋይ አፍሳሾችን እየሳበች ያለችው ኢትዮጵያ ሳትቀር የተከሰተባት ድርቅ እየጸና በሄደበት በአሁኑ ወቅት ከ 15 ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎችዋን ለመመገብ እየታገለች ነው ሲል ዎል ስትሪት ጀርናል ድረ-ገጽ ላይ የወጣው ጽሁፍ ጠቁሟል።

የኒው ዮርክ ታይምስ (New York Times)ጋዜጣ ድረ-ገጽ ደግሞ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የሀገሪቱ ፕረዚዳንት ጃኮብ ዙማ ከስልጣን እንዲወርዱ በመጠየቅ በዋና-ዋና ከተማዎች እንደተሰለፉ ይገልጻል። የታቃውሞው መንስኤ ፕረዚዳንት ዙማ ባለፈው ሳምንት ወሳኝ የሆነ ሹመት ማድረጋቸው በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያላቸው አያያዝ ስጋት በማሳደሩ እንደሆነ ዘገባው ገልጿል።

በኬፕ ታውን፣ በጆሀንስበርግ፣ በፕሪቶርያ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ተቃውሞ ያካሄዱት ሰዎች ገዢው የአፍሪቃ ብሄራዊ ኮንግረስ ዙማን ከስልጣን እንዲያነሳ ጠይቀዋል። ዙማ ስልጣን ከያዙበት ጊዜ አንስቶ በቅሌቶችና በሙስና ተከታታይ ክስ ሲቀርብባቸው የቆየ ቢሆንም ገዢው ፓርቲ ከጎናቸው እንደቆመ ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ድረ-ገጽ ጠቅሷል።

ፕረዚዳንት ዙማ ባለፈው ሳምንት በህዝብ የተከበሩ የገንዘብ ሚኒስትር ናህላንህላ ነነ (Nhlanhla Nene)ን ሳይታሰብ ከስልጣን ባስወገዱበት ወቅት የካቢኔያቸው አባላት ሳይቀሩ እንደተገረሙ ዘገባው አውስቷል። ባለስልጣኑ የፕረዚዳንት ዙማ የቅርብ ወዳጅ ከሆኑት የደቡብ አፍሪቃ የመንግስት አየር መንገድ ሊቀምንበር ከሆኑት ዱዱ ሚየኒ ጋር ተጋጭተው እንደነበር ዘገባው ጨምሮ ጋልጿል።

ፕረዚዳንቱ ዴቪድ ቫን ሩየን የተባሉ በመንግስት ገንዘብ አያያዝ ላይ ልምድ የሌላቸውና ብዙም የማይታወቁ የምክር ቤት አባልን ነነ (Nene) ን እንዲተኩ ሰየሙ። መዋዕለ ነዋይ አፍሳሾች ከባድ ስጋት ካሰሙ በኋላ ራንድ የተባለው የሀገሪቱ ገንዘብ ዋጋ ቁልቁል ወረድ። ፕረዚዳንቱ ታድያ የሰየምዋቸውን ሰው አውርደው በፊት የገንዘብ ሚኒስትር የነበሩት ፕራቪን ጎርዳንን ለመሾም ተገደዱ።

ኮሳቱ የተባለው ከፍተኛ ተደማጭነት ያለው የሰራተኞች ማህበር መሪ የነበሩት የቀድሞ የዙማ ወዳጅ ዝዌልንዚማ ቫቪ ሳይቀሩ ፕረዚዳንት ዙማ ከስልጣን እንዲወርዱ ጥሪ አድርገዋል ሲል ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ላይ የወጣው ዘገባ ጠቁሟል።

ከዚህ በላይ የተዘረዘሩትን ርእሶች አጠናቅራ ባልደረባችን አዳነች ፍሰሃየ ያቀረበችውን ዝግጅት ለማዳመጥ የድምጽ ፋይሉን ይጫኑ።

በኦሮሚያ የሚካሄደው እንቅስቃሴ እና ሌሎች ርእሶች በአፍሪቃ በጋዜጦች
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:53 0:00

XS
SM
MD
LG