38ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ቅዳሜ እና እሁድ በአዲስ አበባ ይካሔዳል፡፡ ለጉባኤው አጀንዳ የሚዘጋጅበት የኅብረቱ ሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ዛሬ ተጀምሯል፡፡
የዘንድሮው 38ኛ ጉባኤ የሚካሔደው ቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የነበረው ኅብረቱ ከተመሰረተ ከ62 ዓመት በኋላ ነው፡፡
በ1994 ዓ.ም ወደ አፍሪካ አንድነት የተቀየረው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣ በወቅቱ ከቅኝ ግዛት ነጻ በነበሩ 32 አገራት መሪዎች በ1955 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ነው የተመሰረተው፡፡
የተዋሃደች፣ ነፃነት፣ እኩልነትና ፍትህ የነገሰባት አፍሪካን እውን የማድረግ ራዕይን አንግቦ የተቋቋመው የመጀመሪያው አህጉራዊ ድርጅት፣ በተቋቋመበት ወቅት ከተከናወኑ ተግባራት አንዱ በ32ቱ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች የዛፍ ችግኞችን መትከል ነው፡፡
ድርጅቱ ከተመሰረተበት አዳራሽ (የአሁኑ የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን) ፊት ለፊት በሚገኝ ስፍራ ላይ በወቅቱ የተተከሉት ችግኞቹ፣ ከ62 ዓመታት በኋላ አሁን ላይ ከከተማዋ መስህቦች መካከል ናቸው፡፡ ስፍራው አፍሪካ ፓርክ በመባል ይታወቃል፡፡
38ኛውን የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ምክንያት በማድረግ በአፍሪካ ፓርክ የሚገኙ በአፄ ኃይለ ሥላሴ፣ ክዋሜ ንክሩማህ፣ ጆሞ ኬንያታ እና ሌሎች የኅብረቱ መስራች መሪዎች የተተከሉትን ዛፎች እናስቃኛችሁ፡፡
መድረክ / ፎረም