የአየር ንብረት ለውጥ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቋቋም የሚያስችል እርምጃ ለመውሰድ እየተደረገ ያለው ጥረት እንቅፋቶች እያጋጠሙት መሆኑ ተሰማ።
ፖላንድ ካቶቪፀ ከተማ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ሃያ አራተኛው የዓለም አየር ንብረት ጉባዔ ሃሣብ ወደፊት እንዳይገፋ እክል የፈጠረው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተደገፈውን የዓለምን ሙቀት ማሻቀብ የሚያሳይ ሪፖርት ለመቀበል ያንገራገሩ ቁልፍ የሚባሉ ሃገሮች መኖራቸው መሆኑ ተገልጿል።
ቁጥራቸው የበዛ በድኅነት ውስጥ ያሉ የአፍሪካና የደቡብ እሥያ ሃገሮች የአየር ንብረት ለውጡ አሁን እያደረሰባቸው ባለው ጉዳት እየተሰቃዩ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ሃገሮቹ እያቀረቧቸው ባሉ ሪፖርቶች የበረታ የውኃ እጥረትና እጅግ የጠነከሩ ማዕበሎች በአካባቢዎቹ ውስጥ መኖር ከዕለት ወደ ዕለት እየከበደ እንዲመጣ ማድረጋቸውን እያመለከቱ ሲሆን በጉባዔ ላይ እየተሣፉ ያሉ የዓለም ሳይንቲስቶችም በለውጡ እየተጎዱ ያሉት ድኆቹ ሃገሮች መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በዓለም በውኃ እጥረት እጅግ ተጎጂ ናቸው ከተባሉት ሃገሮች ሱዳን፣ ኒዠር እና ፓኪስታን ቀዳሚዎቹ መሆናቸውን ዋተር ኤድ የሚባለው ግብረሰናይ ድርጅት አስታውቋል።
ምንም እንኳ ድኆቹ ሃገሮች ለውጡን መቋቋም ለሚያስችሏቸው ፕሮጀክቶቻቸው የሚያውሉት የመቶ ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለመስጠት ከበርቴዎቹ ሃገሮች ቀደም ሲል ቃል ቢገቡም ቃላቸውን ግን እየጠበቁ አለመሆናቸውን ዋተር ኤድ አክሎ ጠቁሟል።
በፓሪሱ የአየር ንብረት ስምምነት መሠረት የዓለም የሙቀት መጠን በያዝነው ምዕት ዓመት መጨረሻ የኢንዱስትሪ አብዮት ከተጀመረበት ጊዜ ከ1.5 ዲግሪስ ሴልሽየስ በላይ እንዳይጨምር ለማድረግ የተያዘውን ጣሪያ ለመጠበቅ በመጭዎቹ 11 ዓመታት ውስጥ የተቃጠለ ጋዝ /ካርበን ዳይኦክሳይድ/ ልቀት መጠን በ45 ከመቶ መቀነስ እንደሚኖርበት ጠቢባኑ እየጎተጎቱ ናቸው።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ