ዩጋንዳ ውስጥ ሲዛመት የከረመው የኢቦላ ወረርሺኝ በቁጥጥር ስር እየዋለ ነው ሲል ዋናው የአፍሪካ የህዝብ ጤና ጥበቃ ተቋም ዛሬ አስታወቀ፡፡
በሀገሪቱ የመጨረሻው ለቫይረሱ የተጋለጠ ሰው ከተመዘገበ 39 ቀናት በማለፉ መሆኑን አስረድቱዋል፡፡
የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል ተጠባባቂ ዳይሬክተር አህመድ ኦግዌል ኡማ ለጋዜጠኞች ባደረጉት ገለጻ አስካለፈው እስከ መጪው የአውሮፓውያን ጥር 10 ቀን ድረስ አንድም የኢቦላ ታማሚ ካልተገኘ ወረርሺኙ ተወገደ ማለት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
እስካሁን ዩጋንዳ ውስጥ በኢቦላ መያዙ የተረጋገጠው ሰው ቁጥር 142 መሆኑን የገለጡት የአፍሪካ ሲዲሲው ባለሥልጣን ሃምሳ አምስት ሰዎች መሞታቸውን አመልክተዋል፡፡
ለሱዳኑ የኢቦላ ቫይረስ ዝርያ ተሰራው የመከላከያ ክትባት ሙከራ እንደቀጠለ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡