በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአፍጋኒስታኑ የመስጊድ ፍንዳታ 18 ሰዎች ተገደሉ


 የታሊባን ወታደር ከደረሰው ፍንዳታ በኋላ፣ አፍጋኒስታን
የታሊባን ወታደር ከደረሰው ፍንዳታ በኋላ፣ አፍጋኒስታን

በምዕራብ አፍጋኒስታን በሰው ብዛት በተጨናነቀ መስጊድ ውስጥ አንድ አጥፍቶ ጠፊ ዛሬ ዓርብ ባደረሰው የቦምብ አደጋ 18 አማኞች ሲገደሉ ቢያንስ 24 መቁሰላቸው ተነገረ፡፡

ከተገደሉት ውስጥ ለታሊባን ታማኝ መሆናቸው የተነገረው ሙጂበር ራህማን አንሳሪ የተባሉት ከፍተኛ የሃይማኖት መሪ እንደሚገኙበት ተዘግቧል፡፡

የታሊባን ዋና ቃል አቀባይ ዛቢሁላህ ሙጃይድ ድርጊቱን አውግዘው ተጠያቂዎቹ ወደ ፍርድ ይመጣሉ ብለዋል፡፡

ቃል አቀባዩ በትዊት መልዕክታቸው “የአገሪቱ ጀግናና ተጽዕኖ ፈጣሪ መምህር ጭካኔና ፍርሃት በተሞላበት ሁኔታ ተገድለዋል” ሲሉ በአንሳሪ ሞት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል፡፡

አንሳሪ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በዩናይትድ ስቴትስ የተመራው የምዕራባውያን ኃይል በአፍጋኒስታን መሰማራቱን ሲቃወሙ መቆየታቸው ተመልክቷል፡፡

ስለ ጥቃቱ ኃላፊነቱን እስካሁን የወሰደ አልተገኘም፡፡

ይሁን እንጂ “አይሲስ ኬ” እየተባለ የሚጠራውና ራሱን በአፍጋኒስታን የእስላማዊ መንግሥት ቅርንጫፍ አድርጎ የሚወስደው ቡድን ተጠያቂ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡

ቡድኑ በቅርብ ወራት በአፍጋኒስታን በሚገኙ በርካታ መስጊዶችና የታሊባን ደጋፊ በሆኑ የሃይማኖት መሪዎች ላይ ጥቃት ሲያደርስ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

XS
SM
MD
LG