ደቡባዊ አፍጋኒስታን ካንዳሃር ከተማ ውስጥ በሚገኝ የታሊባን የፖለቲካ ጉዳዮች ዋና ጽሕፈት ቤት ላይ ዛሬ ሐሙስ ማለዳ በደረሰ የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት ቢያንስ ሦስት ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል፡፡ በአሁኑ ወቅት ያልተለመደ በሆነው ጥቃት ከአስር የሚበልጡ ሌሎች ሰዎች መቁሰላቸው ታዉቋል፡፡
የታሊባን ባለሥልጣናት በሰጡት ቃል አጥፍቶ ጠፊው በላዩ የታጠቀውን ቦምብ ያፈነዳው ደሞዝ የሚቀበሉ ሰዎች በአዲሲቱ ካቡል ባንክ ደጃፍ ተሰልፈው እየተጠባበቁ ሳሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለጥቃቱ እስካሁን ኃላፊ ነኝ ያለ ወገን የለም፡፡ በአደባባይ የማይታዩት የታሊባን ከፍተኛ መሪ ሂባቱላ አኽሁንዛዳ የሚኖሩት አክራሪው ቡድን በተመሰረተባት ካንዳሃር ሲሆን አፍጋኒስታንን በሙሉ የሚያስተዳድሩት እዚያው ሆነው ነው፡፡ ወንዶች ብቻ ያሉበት ካቡል የሚገኘው የታሊባን መንግሥት ሥራው ከከተማዋ ብዙም የማይወጡት አኹንዳዛ ከካንዳሃር በየጊዜው የሚያስተላልፉትን አዋጅ ተግባራዊ ማድረግ ብቻ ነው፡፡
የታሊባኑ መሪ ልጃገረዶች ከስድስተኛ ክፍል በላይ ትምህርት እንዳይማሩ እንዲሁም ሴቶች በመንግሥትም ሆነ በግል ድርጅቶች አንዳይሰሩ መከልከላቸው ይታወሳል፡፡
መድረክ / ፎረም