በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሰሜን አፍጋኒስታን ምክትል አስተዳዳሪ በተሽከርካሪ ላይ በተጠመደ ቦምብ ተገደሉ


በአፍጋኒስታን የሰሜን ምሥራቅ ባዳክሻን የድንበር ግዛት ምክትል አስተዳዳሪን ጨምሮ ሁለት ሰዎች፣ በተሽከርካሪ ላይ የተጠመደ ቦምብ በአስከተለው ፍንዳታ መገደላቸውን፣ የታሊባን ባለሥልጣናት አስታወቁ።

ጥቃቱ የደረሰው፥ ምክትል አስተዳዳሪው ሞልቪ ኒሳርአሕማድ፣ በግዛቲቱ ዋና ከተማ ፌይዛባድ ውስጥ፣ ወደ ሥራ እየተጓዙ የነበሩበት መኪና፣ አጥፍቶ ጠፊ ቦምብ ከተጠመደበት ተሽከርካሪ ጋራ በተላተመበት ወቅት እንደኾነ፣ የአካባቢው ባለሥልጣናት ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

በተሽከርካሪዎቹ ግጭት የተፈጠረው ኃይለኛ ፍንዳታ፣ ምክትል አስተዳዳሪውንና ሌሎች ሁለት ግለሰቦችን ከመግደሉ በተጨማሪ፣ ስድስት ሰላማዊ ሰዎችን ማቁሰሉን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡

ቻይናን፣ ፓኪስታንና ታጂኪስታንን በምታዋስነው የአፍጋኒስታን ተራራማ ግዛት ለደረሰው ጥቃት፣ ለጊዜው ሓላፊነት የወሰደ ቡድን የለም።

ባለፈው ታኅሣሥ ወር፣ የባዳክሻኑ የታሊባን ፖሊስ አዛዥ፣ በተመሳሳይ ኹኔታ ለተገደሉበት በተሽከርካሪ ላይ የተጠመደ የቦምብ ጥቃት፣ ኮሆርሳን ወይም አይኤስ-ኬ በመባል የሚታወቀው የእስላማዊው ጽንፈኛ ቡድን አይሲስ የአፍጋን ቅርንጫፍ ቡድን፣ ሓላፊነት መውሰዱ ይታወሳል።

ታሊባን፣ አፍጋኒስታንን ዳግም ከተቆጣጠረና ያችን አገር ማስተዳደር ከጀመረበት፣ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ፣ አይኤስ-ኬ ሓላፊነት በወሰደባቸው ጥቃቶች፣ በርካታ የታሊባን ከፍተኛ አመራሮች መገደላቸው ተዘግቧል።

XS
SM
MD
LG