ሌሎች አምስት ሰዎች በተገደሉበት ባለፈው ጥር ዘጠኝ ቀን በተካሄደ ድንገተኛ ጥቃት የተያዙትንና ከአንድ ወር ተኩል በላይ በቁጥጥሩ ሥር የቆዩትን እነዚህን ጀርመናዊያን አርዱፍ ባወጣው መግለጫ ይቅርታ መጠየቁን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል፡፡
“የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር - አርዱፍ” ነኝ የሚለው ይህ አማፂ ቡድን ሁለቱን ጀርመናዊያን ለአካባቢው የሃገር ሽማግሌዎች ማስረከቡንም መግለፁ መዘገቡ ይታወሣል፡፡
የፈረንሣዩ የዜና አውታር አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ባወጣው ዘገባ ደግሞ ቁጥራቸውን በውል ያልገለፃቸው የጀርመን ኤምባሲ ባለሥልጣን ወይም ባለሥልጣናትም ሁለቱን ጀርመናዊያን ከሃገር ሽማግሌዎቹ ጋር በአንድ የአፋር ምድረ በዳ ተገኝተው መረከባቸውን አመልክቷል፡፡
ተጠላፊዎቹ ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ ከዓለም እጅግ ሞቃት ሥፍራዎች አንዱ ነው በሚባለው አካባቢ እጅግ በከበደ በረሃማ የአየር ንብረት ውስጥ መቆየታቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በአካባቢው ለመንቀሣቀስ እንዳይቻል በማድረጉ ምክንያት ታጋቾቹን ቀደም ብለው ለማስረከብ ሣይመቻቸው መቅረቱን አማፂያኑ መግለፃቸው በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
ስለጉዳዩ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሕዝብ ዲፕሎማሲና የግንኙነቶች ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ረዳ ለቪኦኤ በሰጡት መግለጫ ስለሰዎቹ መለቀቅም ሆነ ተይዘውም ቢሆን ስለሚገኙበት ሁኔታ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡
በጠለፋው ውስጥ የኤርትራ መንግሥት እጅ አለበት በሚለው አቋሙ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደፀና መሆኑን ያመለከቱት አቶ ጌታቸው አርዱፍ የሚባለው ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ በሕጋዊነት ተመዝግቦ የሚንቀሣቀስ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በአካባቢውም አንዳችም ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንደሌለ የሚናገሩብ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ቃልአቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ሰዎቹን ለማስለቀቅ የኢትዮጵያ መንግሥት የያዘውን ጥረት እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የአፋር ሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ፕሬዚዳንት አቶ ጋአስ አሕመድ ኑር ሁለቱ ጀርመናዊያን መለቀቃቸውን የሚያረጋግጥ የቅርብ መረጃ እንዳላቸው ለቪኦኤ ተናግረዋል፡፡
የጀርመንን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያነጋገረው ሮይተርስ እንደሚለው ደግሞ ሚኒስቴር መ/ቤቱ በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር አይፈልግም፡፡
በጉዳዩ ላይ በቪኦኤ የተላለፈውን ዘገባ እና ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከአፋር ሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ባለሥልጣናት የተደረጉትን የተናጠል ቃለ ምልልሶች ያዳምጡ፡፡