በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአፋር መፈናቀል ይሰማል፤ አስተዳደሩ አስተባብሏል


የአፋር ሰብዓዊ መብቶች ድርጅት በአፋር ክልል ውስጥ ይስተዋላል የሚለውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት አስመልክቶ ተደጋጋሚ መግለጫዎችን ማውጣቱን ሰሞኑን በበተነው የፕሬስ መግለጫ አስታውቋል፡፡

መግለጫው ሲጀምር “ለሃገር ውስጥና ለውጭ መገናኛ ብዙኃን ዝግ በሆነው በአፋር ክልል ውስጥ ብዙ የጭካኔ አድራጎቶችና የመብቶች ረገጣዎች” እንደሚካሄዱ፣ እነዚህ በአፋር ሲቪሎች ላይ ይፈፀማሉ ያላቸው “በደሎች ሳይገለጡና ሳይዘገብባቸው” እንደሚቀሩም አመልክቷል፡፡

“ምንም እንኳ በቅርቡ በኤርታአሌ አካባቢ የውጭ ሃገር ጎብኚዎች መገደላቸውና መጠለፋቸው የዓለምን ትኩረት ወደክልሉ ቢስብም መንግሥት በዞን ሁለት ሲቪሎች ላይ እያካሄደ ያለው የበቀል እርምጃና ወከባ ግብ ብዙም ትኩረት አልተሰጠውም” ይላል የሰብዓም መብቶች ድርጅቱ መግለጫ፡፡

በዞን ሁለት የጅምላ እሥራት እየተካሄደ መሆኑን፣ ሠራተኞች ተቃዋሚዎችን ትደግፋላችሁ እየተባሉ ከሥራ እንደሚባረሩ ይኸው መግለጫ ጠቁሟል፡፡

በአዋሽ ሸለቆ ላይ በተዘረጉትና በሁለት ግድቦች ውኃ በሚጠጡት የሸንኮራ አገዳ ሰፋፊ እርሻዎች ሣቢያ ቁጥሩ እጅግ የበዛ ሰው እየተፈናቀለ መሆኑ በመግለጫው ላይ ከሠፈሩ ሌሎችም ክሦች መካከል ይገኛል፡፡

ቪኦኤ በስልክ ያነጋገራቸው በአፋር ክልል በተባሉት አካባቢዎች ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ሰዎች የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቱ የተጠቀሱትን ክሦች የሚያጠናክሩ ሲሆን ለቪኦኤ ጥያቄዎች መልስ የሰጡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አማካሪ አቶ አሊ አብደላ አሊ የተባሉትን አቤቱታዎች አስተባብለዋል፡፡

ዝርዝሩን ከቅንብሩ ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG