ከአጎራባች የትግራይ ክልል ወረዳዎች ወደ አፋር ክልል ተሻግረዋል የተባሉና ማንነታቸው በግልጽ ያልተለዩ ታጣቂዎች፣ ባለፈው ዕረቡ፣ ግንቦት 13 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ በአፋር ክልል መጋሌ ወረዳ ፈጸሙት በተባለ ጥቃት፣ ሦስት ሰዎች መገደላቸውን፣ ለአሜሪካ ድምፅ በስልክ አስተያየታቸውን የሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የትግራይ ደቡባዊ ዞን አስተዳዳሪ ኣቶ ሃፍቱ ኪሮስ ግን፣ ከክልሉ ወሰን ተሻግረው አፋር ውስጥ ጥቃት የፈጸሙ ታጣቂዎች እንደሌሉ ተናግረዋል።
የአፋር ክልልም ኾነ የፌደራሉ መንግሥት፣ ደረሱ የተባሉትን ጥቃቶች አላረጋገጡም፤ ግድያዎቹን ስለፈጸሙት ታጣቂዎች ማንነትም የሰጡት መግለጫ የለም።
በጉዳዩ ላይ፣ የአሜሪካ ድምፅ፣ በየደረጃው ካሉ የፌዴራል መንግሥት እና የአፋር ክልል አመራሮች ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረትም አልተሳካም።
ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።
መድረክ / ፎረም