በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአፋር ክልል የፈነዳ የሞርታር ጥይት አራት ሰዎችን ገደለ


በአፋር ክልል የፈነዳ የሞርታር ጥይት አራት ሰዎችን ገደለ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:05 0:00

በአፋር ክልል የፈነዳ የሞርታር ጥይት አራት ሰዎችን ገደለ

· “ያልመከኑ ተተኳሾች በየቦታው ኅብረተሰቡን እያወኩ ነው” - /ኦቻ/

በአፋር ክልል፣ አውሲ ረሱ ዞን፣ አድአር ወረዳ፣ ካሳጊታ ከተማ፣ ትላንት ኀሙስ፣ የሞርታር ጥይት ፈንድቶ አራት ሰዎችን መግደሉንና በአምስት ሰዎች ላይ ከባድ እና ቀላል ጉዳት ማድረሱን፣ የዐይን እማኞች ገለጹ፡፡

አካባቢው፣ በቅርቡ የሰላም ስምምነት የቆመው ጦርነት ሲካሔድ የቆየበት መኾኑን የጠቀሱት የከተማዋ ነዋሪዎች፣ “በየቦታው የተጣሉና የተቀበሩ ተተኳሾች እና ፈንጂዎች በሚያስከትሉት ጉዳት፣ የንጹሐን ሕይወት እያለፈ ነው፤” ብለዋል፡፡ አካባቢያቸው ከስጋት ነፃ እንዲኾን፣ በልዩ ልዩ ጊዜያት ለአካባቢያቸው መንግሥታዊ አመራር ቢያሳውቁም፣ ችግሩ መፍትሔ ሳያገኝ መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡

የካሳጊታ ወረዳ ጸጥታ ዘርፍ በበኩሉ፣ ፍንዳታው የተከሠተው፥ የወዳደቁ ብረታ ብረት ሰብሳቢዎች፣ ተጥለው የቀሩ ተተኳሾችን እየቀጠቀጡ በነበረበት ወቅት እንደኾነ አስታውቋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባባሪያ ቢሮ(OCHA) ባወጣው ሪፖርት፣ ጦርነቱ በተካሔደባቸው የሰሜን ኢትዮጵያ ክፍሎች፣ በየቦታው የተጣሉና እንዲመክኑ ያልተደረጉ ተተኳሾች፣ የማኅበረሰቡን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ እያወኩ እንደሚገኙ ገልጿል፡፡

የካሳጊታ ከተማ ነዋሪ የኾኑት ሁመድ መሐመድ፣ በከተማ ውስጥ ተጥሎ የቆየ የሞርታር ጥይት፣ ትላንት ኀሙስ፣ ግንቦት 3 ቀን 2015 ዓ.ም. ፈንድቶ፣ አራት ሰዎች ወዲያውኑ መሞታቸውን ተናግረዋል፡፡

ስለ ፍንዳታው፥ የከተማዋ ነዋሪዎች እና የወረዳው ጸጥታ ዘርፍ፣ የተለያዩ መንሥኤዎችን ይጠቅሳሉ፡፡

የከተማዋ ነዋሪ አቶ ሁመድ፣ ለፍንዳታው ምክንያት ያደረጉት፣ የአካባቢውን ከፍተኛ ሙቀት ነው፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን የሰላም እና ጸጥታ ምክትል መምሪያ ሓላፊ ኮሎኔል ሑሴን አሕመድ፣ የካሳጊታውን ፍንዳታ መንሥኤ ባይጠቅሱም፣ ተተኳሾች በአግባቡ ካልተቀመጡ፣ በከፍተኛ ሙቀት ሊፈነዱ የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡

ከሟቾቹ አንዱ የቅርብ ቤተሰባቸው እንደኾነ የሚናገሩት ዓሊ ለበን የተባሉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ፣ “ፍንዳታው የተፈጠረው በግለሰብ በመነካካቱ ነው፤” ብለዋል፡፡

የካሳጊታ ወረዳ ጸጥታ ዘርፍ ተወካይ ኒበሌ አሊ ግን፣ በአካባቢው ማኅበረሰብ “ቆራሊዮ” በመባል የሚታወቁት የወዳደቁ ብረታ ብረት ሰብሳቢዎች፣ የሞርታር ጥይቱን ሲቀጠቅጡ ፍንዳታው መድረሱን ይገልጻሉ፡፡ በፍንዳታው አራት ሰዎች መሞታቸውንና በአምስት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን አረጋግጠዋል፡፡

አስተያየት ሰጪው አቶ ሑመድ፣ የትላንቱ ፍንዳታ በከተማው ደረጃ ሲከሠት፣ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደኾነ ጠቁመዋል፡፡

የተቀበሩ እና ተጥለው የቀሩ ፈንጂዎች እና ተተኳሾች እንዲመክኑላቸውና እንዲጸዱላቸው፣ ለአካባቢው መንግሥታዊ አካል በተደጋጋሚ ማሳወቃቸውን የሚገልጹት አቶ ሑመድ፣ መፍትሔ እንዳልተሰጣቸው ጠቁመዋል፡፡

የ12ኛ ክፍል ተማሪ መኾኑን የሚናገረው የከተማዋ ነዋሪ መሐመድ አቡከር በበኩሉ፣ ትምህርት ቤቶች፣ የጦር ካምፕ እና የጦር መሣሪያ ማከማቻ ኾነው በመቆየታቸው፣ ሕፃናት በት/ቤቶች ውስጥ በነፃነት ለመንቀሳቀስ እየፈሩ መኾናቸውን አመልክቷል፡፡ ይህም፣ በመማር ማስተማሩ ሒደት ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን አክሏል፡፡

ነዋሪዎች፣ በስጋት ከቤታቸው የማይወጡበት አጋጣሚም እንዳለ መሐመድ ይናገራል፡፡

ስጋቱ፣ “በተገለጸው ልክ አይደለም፤” የሚሉት፣ የወረዳው ጸጥታ ዘርፍ ተወካይ አቶ ነበሌ፣ መከላከያ አካባቢውን ከፈንጂዎች የማጽዳት ሥራ መሥራቱን ገልጸዋል፡፡ “ያልታዩትንና የወዳደቁትን ደግሞ የማጽዳቱ ሥራ ይቀጥላል፤” ብለዋል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበርያ ቢሮ(OCHA)፣ ትላንት ባወጣው ሪፖርቱ፣ በተለይም የግብርና ሥራዎች በሚከናወኑበት፤ የተዘጉ ት/ቤቶችን የማስጀመር እንቅስቃሴ በሚደረግባቸውና ከዚኽ ቀደም ጦርነት በነበረባቸው የሰሜኑ አካባቢዎች፣ በየቦታው የተጣሉና እንዲመክኑ ያልተደረጉ ተቀጣጣዮች፣ የማኅበረሰቡን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ አውከውታል፤ ብሏል፡፡

የአፋር ክልል አውሲ ዞን አድአር ወረዳን በምሳሌነት ያነሳው ኦቻ፣ በሚያዝያ ወር ብቻ፣ አራት ፍንዳታዎች መድረሳቸውን የሚያረጋግጡ ሪፖርቶች እንደደረሱት አመልክቷል፡፡ በተመሳሳይም፣ በዐማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ጋሸና አካባቢ፣ በሰዎች ላይ ጉዳት ያደረሱ ተመሳሳይ 15 ፍንዳታዎች መከሠታቸውን፤ በትግራይ ክልል ደግሞ፣ ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ በ41 ሰዎች ላይ ጉዳት ሕክምና መውሰዳቸውን ጠቅሷል፡፡

የካሳጊታ ከተማ አስተያየት ሰጭዎች፣ ማኅበረሰቡ ስለ ተተኳሾቹ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ ነው፤ ይላሉ፡፡

ተተኳሾችን አስመልክቶ፣ በሦስቱም ክልሎች ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ኦቻ በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ ያም ኾኖ የስጋት ቀጣና የኾኑ አካባቢዎችን ማጽዳት፣ አንገብጋቢ ተግባር እንደኾነ በሪፖርቱ አሳስቧል፡፡

XS
SM
MD
LG