በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢሰመኮ የሽብር ወንጀል ተከሣሾችን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አቤቱታ መርምሮ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤት አዘዘ


ኢሰመኮ የሽብር ወንጀል ተከሣሾችን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አቤቱታ መርምሮ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤት አዘዘ
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:08 0:00

ኢሰመኮ የሽብር ወንጀል ተከሣሾችን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አቤቱታ መርምሮ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤት አዘዘ

- “የልጅ ልጄ ሊኾን በሚችል ፖሊስ ተደብድቤያለሁ፤ ተገርፌያለሁ” - ዶር. መሠረት ቀለመ ወርቅ

በሽብር ወንጀል የተከሠሡ ግለሰቦች፣ ያቀረቡትን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አቤቱታ አስመልክቶ፣ ኢሰመኮ፥ በ15 ቀናት ውስጥ የምርመራ ውጤት እንዲያቀርብ፣ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

በዐማራ ክልል፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን በመግደል፣ የክልሉን ብሎም የፌዴራሉን ሥልጣን በኃይል ለመቆጣጠር በማሰብ የሽብር ድርጊት ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙ ተከሣሾች፣ በዛሬው ዕለት ችሎት ቀርበዋል፡፡

ተከሣሾቹ፣ በዛሬው ውሎ ለችሎቱ በአሰሙት አቤቱታ፣ “የተፈጸመብንን የሰብአዊ መብት ጥሰት ለማስረዳት፣ ቃላችንን በምንሰጥበት ወቅት፣ ፖሊስ ከኢሰመኮ ባለሞያዎች ጋራ ተገኝቷል፤” በሚል፣ ኹኔታው ጫና እንደተፈጠረባቸው ገልጸዋል፡፡

አቤቱታውን ካሰሙት ተከሣሾች አንዱ ዶር. መሠረት ቀለመ ወርቅ፣ ዕድሜያቸው 67 ገደማ እንደኾነ ጠቅሰው፣ “የልጅ ልጄ ሊኾን በሚችል ፖሊስ ተደብድቢያለኹ፤ ተገርፌያለኹ፤” ካሉ በኋላ፣ ይህንኑ አስመልክቶ፣ ለኢሰመኮ ባለሞያዎች ቃላቸውን በሚሰጡበት ጊዜ፣ ፖሊስም በቦታው እንደነበረ ገልጸዋል፡፡ ድርጊቱ ትክክል እንዳልነበረ የተቹት የኢሰመኮ ባለሞያዎች፣ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡

በእነዶር. ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ፣ ሰኔ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. በዐቃቤ ሕግ የሽብር ወንጀል ክሥ ከተመሠረተባቸው 51 ግለሰቦች መካከል፣ በእስር ላይ የሚገኙት 24ቱ፣ ክሥ ከተመሠረተባቸው በኋላ፣ ዛሬ ዐርብ፣ ሰኔ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. ለሦስተኛ ጊዜ ችሎት ቀርበው ክርክር ተደርጓል፡፡

ባለፈው ሰኞ፣ ሰኔ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. በነበረው ችሎት ላይ፣ በዐቃቤ ሕግ የቀረበው ክሥ፣ በፍርድ ቤቱ ሬጂስትራር ማኅተም ተረጋግጦ እንዲቀርብ፣ እንዲሁም ክሡን ያዘጋጀው ዐቃቤ ሕግ፥ ስም እና ፊርማ

እንዲያርፍበት በቀረቡ ክርክሮች ላይ ብይን ለመስጠት ነበር፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ የፀረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎት፣ ለዛሬ ቀጠሮ የሰጠው፡፡

በቀረበው ክሥ እና መቃወሚያ ላይ የተደረገውን ክርክር፣ ከተከሣሽ ጠበቆች መካከል አንዱ የኾኑት፣ ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ ሰሎሞን ገዛኸኝ አብራርተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ፣ በዛሬው ችሎት፥ ከተከሣሾች የቀረቡ የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን፣ እንዲሁም ሌሎች ከመብት ጥያቄ ጋራ የተገናኙ አቤቱታዎችንም አዳምጧል፡፡

ባለፈው የችሎት ውሎ፣ የኢትየጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፥ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ጉዳዮችን መርምሮ እንዲያቀርብ፣ ትዕዛዝ ሰጥቶ የነበረ ቢኾንም፣ ዛሬ ከኮሚሽኑ የቀረቡ ሦስት ባለሞያዎች፣ “የምርመራ ትዕዛዝ ደብዳቤ ለኮሚሽኑ የደረሰው፣ ባለፈው ረቡዕ፣ ሰኔ 7 ቀን እንደኾነ” ገልጸው፣ በጊዜው ማጠር ምክንያት፣ የምርመራ ውጤቱ እንዳልደረሰላቸው አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ኮሚሽኑ፣ ተደራራቢ የምርመራ ሥራዎች እንዳሉበት፣ የተከሣሾችን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በተመለከተ የሚደረገው ምርመራ ደግሞ፣ ውስብስብ እንደኾነ ጠቅሰው፣ ውጤቱን ለማቅረብ፣ ተጨማሪ የ15 ቀናት ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

ተከሣሾች እና ጠበቆቻቸው በበኩላቸው፣ የ15 ቀን ጊዜ እንደሚበዛና ማስረጃውን ለክሥ መከላከል ተግባር ስለሚፈልጉ፣ በአጭር ጊዜ እንዲደርሳቸው ይደረግ ዘንድ ጠይቀዋል፡፡

በተጨማሪም፣ ለምርመራ ቃል በምንሰጥበት ወቅት፣ ፖሊሶች፥ ከኢሰመኮ ባለሞያዎች ጋራ ኾነው ይከታተሉን ነበር፡፡ ይህም፣ በእኛም በኮሚሽኑም ላይ ጫና የሚያሳድር በመኾኑ፣ እርምት ይደረግበት፤ ሲሉ፣ ሁለት ተከሣሾች አቤቱታ አቅርበዋል፡፡

አቤቱታውን ካሰሙት አንዱ የኾኑት ዶር. መሠረት ቀለመ ወርቅ፣ ዕድሜያቸው 67 ገደማ እንደኾነ ጠቅሰው፣ “የልጅ ልጄ ሊኾን በሚችል ፖሊስ ተደብድቤያለኹ፤ ተገርፌያለኹ፤ ይህን ችሎቱ እንዲያውቅልኝ እፈልጋለኹ፤” ብለዋል፡፡ ይህን አስመልክቶ፣ ለኢሰመኮ ባለሞያዎች ቃላቸውን በሚሰጡበት ጊዜ፣ ፖሊስም በቦታው እንደነበረ ገልጸዋል፡፡

ለዚኽ ምላሽ የሰጡት፣ የኢሰመኮ ባለሞያዎች በበኩላቸው፣ ፖሊስ በወቅቱ በቦታው የነበረው፣ የቅሬታ አቅራቢው ፈቃደኝነት ተጠይቆ፣ ፈቃደኛ በመኾናቸው ነው፤ ብሏል፡፡ ኾኖም፣ ተከሣሹ ቃላቸውን በሚሰጡበት ጊዜ፣ ፖሊስ መኖር እንዳልነበረበትና የኮሚሽኑ አሠራርም እንደማይፈቅድ የተናገሩት የኢሰመኮ ባለሞያዎች፣ ለተፈጠረው ስሕተት ችሎቱን ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ችሎቱ፣ ኢሰመኮ፥ ለተከሣሾች የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ጉዳይ፣ ቅድሚያ ሰጥቶ ምርመራውን እንዲያደርግ በማሳሰብ፣ ውጤቱን፥ ለሰኔ 23 ቀን ከተቻለም ከዚያ አስቀድመው እንደያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ የኢሰመኮ ባለሙያዎችም፣ ኮሚሽኑ ጉዳዩን፥ በፈጣን ምላሽ ፕሮግራሞች ሥር አካቶ በማየት፣ በተባለው ጊዜ አልያም ከጊዜው አስቀድሞ ውጤቱን እንደሚያደርስ አረጋግጠዋል፡፡

ተከሣሾች፣ በዛሬው ችሎት ካነሧቸው ሌሎች ጉዳዮች መካከል፣ የተፋጠነ ፍትሕን የሚጠይቅ ይገኝበታል፡፡ ዘጠነኛ ተከሣሽ የኾነው የብዙኃን መገናኛ ባለሞያው ዳዊት በጋሻው፣ “የፖለቲካ እስረኞች ነን፤ እዚኽ ያለነው ጋዜጠኞች፣ የመብት ተሟጋቾች፣ የሲቪክ ማኅበራት መሪዎች እና ፖለቲከኞች ነን፤” ካለ በኋላ፣ “በእስር እንድንቆይ የተደረግነውም፣ የአገሪቱን ወቅታዊ ኹኔታ እንዳንከታተል ነው፡፡ የዐማራን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ በሚወስኑ ጉዳዮች ላይ እንዳንሳተፍ ተፈልጎ፣ የፍትሕ ሥርዐቱ እየተጓተተ ነው፤” የሚል ቅሬታ አቅርቧል፡፡ መንግሥት፣ በዳኞች ላይ ጫና ሊያሳድር ይችላል፤ የሚል ስጋትም ከእስረኞቹ ተነሥቶ፣ በችሎቱ የተሠየሙት ዳኞች በሰጡት ምላሽ፣ ሥራችንን በነፃነት ነው የምናከናውነው፤ ከዳኝነት ነፃነት አንጻር፣ ምንም ስጋት ሊገባችኹ አይገባም፤ ብለዋል፡፡

ተከሣሾቹ ለቀረበባቸው ክሥ ከተያያዙ ማስረጃዎች መካከል፣ የድምፅ እና ሌሎች ፋይሎችን የያዘ ፍላሽ የሚገኝበት ሲኾን፣ ፍላሹ የተሰጣቸው ተከሣሾች፣ ማስረጃውን ለመመልከት እና ለማድመጥ ይችሉ ዘንድ ግን፣ ወደ እስር ቤቱ ይዘው መግባት እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡ ይህ ለምን እንዳልኾነ የተጠየቁት የፖሊስ ኮማንደር፣ መመሪያቸው፥ ምንም ዐይነት ኤሌክትሮኒክስ ይዞ መግባት እንደማይፈቅድ ጠቅሰው፣ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ በማሳወቅ የጠየቋቸው የበላይ አካላትም ባለመፍቀዳቸው እንደኾነ አመልክተዋል፡፡

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ፣ ተከሣሾቹ የሚገኙባቸው እስር ቤቶች፣ በፍላሽ የተያዙ የድምፅ እና ሌሎች ፋይሎችን ለመመልከት፣ በተለያየ ምክንያት አመቺ ስለማይኾኑ ወይም ምቹ ኹኔታ ስለሌለ፣ ክሡ ተሰምቶ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡

ችሎቱ፣ የዐቃቤ ሕግን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ፣ ተከሣሾቹ ታስረው የሚገኙባቸው የፌዴራል እና የዐዲስ አበባ ፖሊስ ተቋማት፣ ለተከሣሾቹ፣ ፍላሾቹ ላይ ያሉ ፋይሎችን የሚከታተሉበት፣ በቂ ጊዜ፣ ቦታ እና ቁሳቁስ እንዲያመቻቹ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

በ51ዱ ተከሣሾች ላይ፣ በ71 ገጾች የቀረበው የዐቃቤ ሕግ ክሥ፣ ተከሣሾቹ፣ “መነሻችን ዐማራ መድረሻችን ኢትዮጵያ በሚል የፖለቲካ እና የርእዮት ዓላማቸውን ለማራመድ፣ የሽብር ድርጊት ፈጽመዋል፤” ሲል ወንጅሏል፡፡ በዚኽም፣ ከ217 በላይ ለሚኾኑ ሰዎች ሞት ምክንያት እንደኾኑ ያስረዳል፡፡

ከ51ዱ ተከሣሾች መካከል 27ቱ፣ በሌሉበት የተከሠሡ ናቸው፡፡ የዛሬው ችሎት፣ በዐቃቤ ሕግ የቀረበው ክሥ፣ የፍርድ ቤት ሬጂስትራር ማኅተም ተረጋግጦ እንዲቀርብ በተደረገው ክርክር እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ብይን ለመስጠት፣ ለኀሙስ ሰኔ 15 ቀን ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

XS
SM
MD
LG