ዋሺንግተን ዲሲ —
የኖቤል ሎሬት ተሸላሚዋ ማላላ ዩሳፍዛይ ለሴቶች የመማር መብት በመታገሏ በአክራሪው ነውጠኛ ቡድን ታሊባን ጥይት ከተመታች ከሥድስት ዓመት በኋላ ዛሬ ሐሙስ ወደ ትውልድ ሀገሯ መመለሷ ተገለፀ።
የሃያ ዓመቷ ወጣት የመብት ተሟጋቿ ማላላ ኢዝላማባድ አውሮፕላን ጣቢያ ስትደርስ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ሻሂድ ከሃቃን ጋር መገናኘቿም ታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ በተዘጋጀ ልዩ ስብስብ ላይ ስትናገርም፣ “ይሄ ሁሉ እውነት መሆኑን ማመን ያቅተኛል” ብላለች።
ማላላ ከት/ቤት ስትመለስ በታሊባን ጥቃት ደርሶባት ከነበረው በርካታ ጉዳት ለማገገም እዚያው ፓኪስታን ውስጥ ስትረዳ ቆይታ፤ ለበለጠ ቀዶ ህክምና ወደ እንግሊዝ አገር መሄዷ ይታወቃል።
ማላላ፣ ሦርያን፣ ኬንያን፣ ናይጄሪያን፣ ዮርዳኖስንና ፓኪስታንን ጨምሮ፣ በጦርነትና ውዝግብ ውስጥ ያሉ አገሮች ሴቶች የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ በሚል የተቋቋመው “የማላላ ፈንድ” ተባባሪ መሥራች የሆነች መሆኗም ይታወቃል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ