በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አበርገሌ ወረዳ በመከላከያ ቁጥጥር ሥር መዋሉን አስተዳደሩ አስታወቀ


አበርገሌ ወረዳ በመከላከያ ቁጥጥር ሥር መዋሉን አስተዳደሩ አስታወቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:47 0:00

አበርገሌ ወረዳ በመከላከያ ቁጥጥር ሥር መዋሉን አስተዳደሩ አስታወቀ

· “የጻግብጂ ወረዳ አሁንም በህወሓት ታጣቂዎች ሥር ነው” - የወረዳው የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት ሓላፊ

በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ዞን የአበርገሌ ወረዳ፣ በህወሓት ቁጥጥር ሥር እንደነበረ ሲገልጽ የቆየው አስተዳደሩ፣ ወረዳው፣ ከትላንት ጀምሮ በመከላከያ ቁጥጥር ሥር መዋሉን አስታውቋል።

ይህንም ተከትሎ፣ ከኹለት ዓመት ከስድስት ወራት በኋላ ወደ ቀዬአቸው መመለሳቸውን የገለጹ አስተያየት ሰጪዎች፣ ቤተ ሰዎቻቸው ጋራ መገናኘት በመቻላቸው ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።

በሌላ በኩል፣ በዞኑ የሚገኘው የጻግብጂ ወረዳ፣ አሁንም በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ሥር እንደሚገኝ፣ የወረዳው መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት ገልጾ፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀዬቸው በመመለስ፣ መንግሥት ሓላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቋል፡፡

ከዚኽ ቀደም ስለ ጉዳዩ የጠየቅናቸው አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የትግራይ ኃይሎች አመራር በበኩላቸው፣ “የትግራይ ሠራዊት በአማራ ክልል አንድም አካባቢ የለም፤” የሚል ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል።

የአበርገሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ዓለሙ ክፍሌ፣ ተፈናቅለው የነበሩ የመንግሥት አመራሮች እና የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ከትላንት ጀምሮ ወደ ቀዬአቸው መመለስ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

አስተዳዳሪውንና ነዋሪዎቹን በስልክ አነጋገርናቸዋል፡፡ ዳዊት ተሰማ የተባሉ የአበርገሌ ወረዳ ዋና ከተማ ነዋሪ፣ የተለዩዋቸውን እናታቸውን ከኹለት ዓመት ከስድስት ወር በኋላ በአካል በማግኘታቸው ደስታቸውን ሲገልጹ፣ አሳድጋኛለች ያሏቸው አያታቸው በአንጻሩ፣ በሕክምና ዕጦት በሞት መለየታቸውን በመረዳታቸው ኀዘን እንደተሰማቸው ተናግረዋል፡፡

በሰቆጣ መጠለያ ጣቢያ ኾነው ወደ ቀዬአቸው የሚመለሱበትን ጊዜ እየተጠባበቁ መኾናቸውን የተናገሩ፣ አቦነህ በርከፋች የተባሉ አስተያየት ሰጪ፣ የሚበዙት ተፈናቃዮች አሁንም በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ቢኾኑም፣ አካባቢው ከኹለት ዓመት ከስድስት ወር በኋላ ነፃ በመውጣቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ በተለይ

በመፈናቀል ምክንያት፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ ልቡናዊ ጫና ለደረሰበት ኅብረተሰብ፣ የአካባቢው ነፃ መኾን ትርጉም እንዳለው አስተያየት ሰጪው አስገንዝበዋል፡፡

ዋና አስተዳዳሪው አቶ ዓለሙ በበኩላቸው፣ በወረዳው ውስጥ በተለይም በከተማዋ ኒሯቅ የደረሰው ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት የከፋ እንደኾነ አመልክተዋል፡፡ ይኹንና መንግሥታዊ መዋቅሩ፣ ሥራ ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደኾነ ዋና አስተዳዳሪው አረጋግጠዋል፡፡ የተፈናቀለውንም ሕዝብ ወደ ቀዬው ለመመለስ፣ ከመንግሥት እና መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች ጋራ በትብብር እየተሠራ እንዳለ አሳውቀዋል፡፡

አካባቢው፣ የህወሓት ኃይሎች ለረጅም ጊዜ ተቆጣጥረውት የቆዩበትና የጦርነት ቀጣና ከመኾኑ አንጻር፣ ሙሉ በሙሉ ከጸጥታ ስጋት ነፃ እንዳልኾነ በማውሳት፣ ስጋታቸውን የገለጹ አስተያየት ሰጪዎች አልጠፉም።

ኾኖም፣ ዋና አስተዳዳሪው ስለ ጉዳዩ እንዳስረዱት፣ “ጄኔራሎችን ጨምሮ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች በአካባቢው ከነበሩት የህወሓት ታጣቂዎች ጋራ ውይይት በማድረጋቸው በጸጥታው ዙሪያ የሚያሳስብ የለም።” የህወሓት ኃይሎች ተቆጣጥረዋቸው ከነበሩት 14 ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ ለቀው መውጣታቸውን አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

“ጄኔራሎችን ጨምሮ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች በአካባቢው ከነበሩት የህወሓት ታጣቂዎች ጋራ ውይይት በማድረጋቸው በጸጥታው ዙሪያ የሚያሳስብ የለም።”

በሌላ በኩል፣ በጉዳዩ ላይ ከትግራይ ክልል በኩል ምላሽ ለማግኘት፣ መቐለ የሚገኘው ዘጋቢያችን፣ የክልሉን የልዩ ልዩ ቢሮ ሓላፊዎችን ቢያነጋግርም፣አብዛኞቹ፣ “ስለ ጉዳዩ የምናውቀው ነገር የለም፤ ጉዳዩ የሚለከተው የትግራይ ኃይሎችን ነው፤” የሚል ምላሽ ነው የሰጡት።

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የትግራይ ኃይሎች አመራር፣ “የትግራይ ሠራዊት፣ በአማራ ክልል አንድም አከባቢ የለም፤” ብለዋል። ኾኖም፣ በተጠቀሱ የዋግህምራ አካባቢዎች፣ ሌሎች ታጣቂዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።የወረዳው የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት ሓላፊ ጌታወይ ሸሜም፣ በዞኑ የጻግብጂ ወረዳ፣ አሁንም በህወሓት ታጣቂዎች ሥር እንደሚገኝ ነው ያረጋገጡት፡፡

ከወር በፊት፣ የአሜሪካ ድምፅ፣ ከ25 እስከ 30 ሺሕ የሚጠጉ የጻግብጂ ወረዳ ተፈናቃዮች፣ በሰቆጣ እና አካባቢው መጠለያ ጣቢያዎች መስፈራቸውን ቢዘግብም፣ ሓላፊው፣ ቁጥሩ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ እስከ 10ሺሕ ጨምሯል፤ ብለዋል፡፡

በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት፣ ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ በቂ ድጋፍ እንደማይደረግላቸው በማውሳት፣ ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡

XS
SM
MD
LG