አዲስ አበባ —
በአበበች ጎበና የህፃናት እንክብካቤና ልማት ማዕከል ሥልጠና ከወሰዱት ወጣቶች 65 ከመቶው በተለያዩ ድርጅቶች ተቀጥረው የሚሠሩ ሲሆን 15 ከመቶ የሚሆኑት ደግሞ የራሳቸውን ሥራ መፍጠራቸውን፣ ለሌሎችም የሥራ ዕድሎች የከፈቱ መኖራቸውን የማዕከሉ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ይትባረክ ተካልኝ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓሲ በኢትዮጵያዊቱ የበጎ አድራጎት ሰው ዜና ዕረፍት የተሰማቸውን ኀዘን ገልፀዋል።
አምባሳደሯ በአሜሪካዊያንና ኢትዮጵያዊያን ባልደረቦቻቸው ስም ጭምር ባስተላለፉትና በኤምባሲው ዌብሳይት ላይ በሠፈረው የኀዘን መግለጫ የአበበች ጎበናን ሥራዎች አድንቀዋል።
አምባሳደሯ በዚሁ መልዕክታቸው “የአበበች ጎበና ህይወት ምሳሌነትና ስኬቶች ሁላችንንም እያነቃቁ ይቀጥላሉ” ብለዋል።
/ክቡራትና ክቡራን ተከታዮቻችን፤ በቀደመ ዜና “አምባሳደሯ የአበበች ጎበናን ቤተሰብ ጎበኙ” የተባለው ትክክል ስላልሆነ ይቅርታ እየጠየቅን ከዚህ በላይ በሠፈረው የኀዘን መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸውን በሚገልፀው ዜና እንዲታረም ከአክብሮት ጋር እንጠይቃለን።/