ዋሺንግተን ዲሲ —
ሰሜናዊ ኩርዲስታን ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን እና የሕግ የበላይነት እንዲከበር የኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይደር አል አባዲ ተማፀኑ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተማፅዕኖውን ያቀረቡት የክልሉ መሪ ሥልጣናቸውን እንደሚለቅቁ ትናንት ማስታወቃቸውን ተከትሎ ነው።
የኩርዲስታንን ሁናቴና በፓርቲዎች ዋና ፅሕፈት ቤቶች የደረሱትን ጥቃቶች በቅርበት እየተከታተሉ መሆናቸውን ዛሬ ሰኞ ጠቅላይ ሚኒስትር አባዲ አስታውቀዋል።
የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎችንና ኢርቢልና ዳሁክ ውስጥ ረብሻ ለመፍጠር የሚደረጉ ሙከራዎችንም ጭምር እየተከታተልን ነን ብለዋል።
የባግዳዱ ማዕከላዊ መንግሥት በሀገሪቱ ክፍለ ግዛቶች በሙሉ ሰላም እንዲሰፍን እና የሁሉም ዜጎች ጥቅም እንዲከበር የሚፈልግ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።
የኢራቅ ኩርዱ መሪ ማሱድ ባርዛኒ ትናንት ዕሁድ በቴሌቭዥን ባሰሙት ንግግር እኤአ ከተነገ ወዲያ ህዳር አንድ ጀምሬ ሥልጣን እለቃለሁ ሲሉ አስታውቀዋል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ