በሱዳን ምስራቃዊ ቀይ ባህር ግዛት አንድ ግድብ ተደርምሶ ያሰከተለው ጎርፍ መኖሪያ ቤቶችን ማጥለቅለቁን የሀገሪቱ የጤና ሚኒስትር አስታውቋል። በርካታ ሰዎች የደረሱበት እንደማይታወቅም የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ሚኒስቴር መስሪያቤቱ እላንት እሁድ በሰጠው መግለጫ አርባት የተሰኘው ግድብ መደርመሱን እና ከአደጋው መውጫ ያጡ ሰዎችን ለመርዳት እርዳታ ወደአካባቢው መላኩን አስታውቋል።
መግለጫው አክሎ በጎርፍ አደጋው ቢያንስ አራት ሰዎች መሞታቸውን የገለጸ ሲሆን ምን ያክል ሰዎች የደረሱበት እንዳልታወቀ ግን አላብራራም። ሆኖም አንድ የአካባቢው ባለስልጣን ለሱዳኑ የዜና ጣቢያ አል-ታግሂር ቢያንስ 60 ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተናግረዋል። የቀይ ባህር ግዛት የውሃ ሀብት ኃላፊ የሆኑት አሚር ኢሳ ታሂር የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
መዳሚክ የተሰኘው የሱዳን ዜና ማሰራጫ በበብኩሉ የሀገሪቱ ኃይል ጠቅሶ እንደዘገበው ከ100 በላይ ሰዎች የደረሱበት የማይታወቅ ሲሆን ሌሎች በርካታ የመንደሩ ነዋሪዎችም እየጨመረ ከመጣው ውሃ ለመሸሽ ወደ ተራራ ጫፍ መውጣታቸውን አስታውቋል።
ግድቡ ከፖርት ሱዳን ከተማ በስተሰሜን 40 ኪሎ ሜትር (25 ማይል) ርቀት ላይ የሚገኘው አራባት ግድብ ለከተማዋ ንፁህ ውሃ የሚያቀር ነው። ግድቡ ቅዳሜ ምሽት የተደረመሰው በአካባቢው በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት መሆኑን የሀገር ውስጥ ዜና አገልግሎቶች ዘግበዋል።
መድረክ / ፎረም