በዩናይትድ ስቴትስ የፕሬዚዳንታዊው ዘመን አጋማሽ የምክር ቤት አባላት ምርጫ ተጠናቆ ቀጣዩ ትኩረት በ2017 ዓ.ም (የዛሬ ሁለት ዓመት) በሚደረገው ፕሬዚዳንታዊ ፉክክር ላይ ሆኗል፡፡
ባላፈው ሳምንት የዛሬ ሁለት ዓመት በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለሌላ ውድድር መዘጋጀታቸውን ይፋ ያደረጉት የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ፍላጎታቸውን በገለጹበት ምሽት “አሜሪካን እንደገና ታላቅ እናደርጋታለን ፣ እግዚአብሄር ሁላችሁንም ይባርካችሁ” ብለዋል፡፡
ትረምፕ ለዋይት ሀውስ ሲፎካከሩ ይኸኛው ሦስተኛቸው ይሆናል፡፡
ትረምፕ ይህን ይፋ ካደረጉ ጥቂት ቀናት በኋላ የባይደን አስተዳደር ጠቅላይ አቃቢ ህግ ትረምፕ እኤአ ጥር 6/2021 በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ህንጻ ላይ በደረሰው ሁከትና ጥቃት የነበራቸውን ሚና በሚመለከት እና ሥልጣን ከለቀቁም ሁለት ሳምንታት በኋላ ሚስጥራዊ ሠነዶች ተገኝቶባቸው እንደሆነ የሚመለከት ልዩ መርማሪ ሾመዋል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ አቃቢ ህግ ሜሪክ ጋርላንድ ሹመቱን ይፋ ባደረጉበት ንግግራቸው “ዛሬ እዚህ የተገኘሁት የህዝቡን ትኩረት የሳቡትና እየተካሄዱ ካሉ ሁለት የወንጀል ምርመራዎች ጋር በተያያዘ ልዩ መርማሪ መሾሙን ይፋ ለማድረግ ነው፡፡” ብለዋል፡፡
የመርማሪው መሾም ይፋ የተደረገው የፕሬዚዳንታዊው ዘመን አጋማሽ የምክር ቤት አባላት ምርጫ ውጤት ይፋ ከተደረገ በኋላ ነው፡፡
ዴሞክራቶች በጠባብ ውጤት አሸንፈው የህግ መወሰኛውን ምክር ቤት መቆጣጠራቸው ብዙዎችን አስደንቋል፡፡
ሪፐብሊካኖቹም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን የተቆጣጣሩ ቢሆንም ውጤቱ ግን ከተጠበቀው በታች ነው፡፡
ይሁን እንጂ የተከፋፈለ ምክር ቤት ማለት ለዴሞክራቱ ፕሬዚዳንት ጆባይደን በመጨረሻዎቹ ሁለት የሥልጣን ዘመናቸው ህጎችን ለማሳለፍ ብርቱ ፈተና ይሆንባቸዋል ማለት ነው፡፡
ሪፐብሊካኑ የተወካዮች ምክር ቤት አባል ኬቭን መካርቲ “በዋሽንግተን የዴሞክራቱ የአንድ ፓርቲ አገዛዝ ዘመን ማብቃቱን ይፋ ሳደርግ በኩራት ነው” ብለዋል፡፡
በትራምፕ የተደገፉት አንዳንድ የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩዎችጥሩ ውጤት አላመጡም፡፡
ባይደን ካለፈው የበጋ አጋማሽ ጀምሮ ድክመት እንደታየባቸው ተገምቶ ቆይቷል፡፡ የዋጋ ግሽበት ሲያድግ በህዝብ ዘንድ የነበረው የባይደን ተቀባይነትም ከ40 በታች ወርዶ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ አንዳንድ የሪፐብሊካን መሪዎችም ትረምፕ የፓርቲያቸው እጩ እንዲሆኑ የማይፈልጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የቀድሞ የህዝብ ተወካዮች አፈጉባኤ የነበሩት ሪፐብሊካኑ ፖል ራያን “በዚህ ሳምንት” በተሰኘው የኤቢሲ ቴሌቭዥን ፕሮግራም ላይ ይህንኑ ሲገልጹ “ምናልባት ትረምፕ ከሆኑ ዋይት ሀውስን ልናጣ እንችላለን፡፡ ትምረፕ ብቻ አይሁን እንጂ ሌላ ዕጩ ቢቀርብ የኔ ግምት ዋይት ሀውስን እናሸፋለን የሚል ነው፡፡” ብለዋል፡፡
በዚህ ሳምንት ከ15 ሚሊዮን ህዝብ በተወሰደ አስተያየት ድምጽ የትዊተር ሥራ አስፈጻሚ ኢላን ማስክ ታግዶ የነበረውን የትረምፕ የትዊተር አካውንት ፈቅደዋል፡፡
እኤአ በ2021 በምክር ቤቱ ህንጻ ላይ ከተካሄደው ጥቃት በኋላ ትዊተር ትረምፕ መድረኩን እንዳይጠቀሙ ከልክሎ ነበር፡፡
ላሁኑ ግንተፈቅዷል፡፡ ትረምፕም “ትሩዝ” (እውነት) የተሰኘው የማህበራዊ መገናኛ መድረካቸውን ብቻ መጠቀም እንደሚቀጥሉ ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡