በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ህግ አውጭዎች ትራምፕን ከሥልጣን ስለማባረር እየተወያዩ ነው


ተመራጩ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የፕሬዘደንትነት ሥልጣን ፣ እኤአ ጃንዋሪ 20 በይፋ ይጀምራል፡፡ በዚሁ እለትም በዓለ ሲመታቸውን ለማክበር በዝግጅት ላይ ይገኛሉ፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ የተወካዮች ምክር ቤት፣ ባለፈው ረቡዕ ከነበረው አመጽ ጋር ተያይዞ በነበራቸው ሚና ፣ ተሰናባቹን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን፣ ለሁለተኛ ጊዜ ከሥልጣናቸው ሊያስወግዳቸው ይገባል ወይስ አይገባም የሚለው ጥያቄ እያከራከረ ነው፡፡

በፕሬዚዳንት ትራምፕ ደጋፊዎች የተነሳውና፣ አምስት ሰዎች የሞቱበት፣ ያለፈው ሳምንቱ አመጽ፣ አሁንም እያነጋገረ ነው፡፡ ህግ አውጭዎቹ የምክር ቤት አባላት፣ አመጹን አነስተተዋል ያልዋቸውን ፕሬዚዳንት ትራምፕን ከሥልጣን እንዲወገዱ የሚያዘውን ውሳኔ፣ ለሁለተኛ ጊዜ ለማሳለፍ መወያየት ይዘዋል፡፡

ትራምፕ፣ ባለፈው ሳምንት፣ ከጥቃቱ በፊት ለደጋፊዎቻቸው ባሰሙት ንግግር፣ ምርጫው የተጭበረበረና፣ ውጤቱም የተሰረቀባቸው መሆኑን ገልጸው፣ ይህንኑ በመቃወም ፣ወደ ምክር ቤቱ ህንጻ እንዲገሰግሱ አሳሰባዋቸዋል፡፡

በነጋታው ሀሙስ፣ የዋይት ኃውስ የፕሬስ ቃል አቀባይ ባወጣው መግለጫ፣ ትራምፕ በአመጹ የተፈጸመውን ጥቃት ማውገዛቸውን አስታውቋል፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሆኑት፣ የኒዮርኳ አሌክሳንድሪያ ኦካስዮ ኮርቴዝ ግን፣ ፕሬዚዳንቱ ከሥልጣን መወገድ እንዳለባቸው እንዲህ በማለት ይናገራሉ

“እንግዲህ እኔ፣ ፕሬዚዳንቱን ከሥልጣናቸው የሚያባርር ውሳኔ የሚወሰድበት መረሀግብር መውጣት እንዳለበት የሚያሳዩ፣ ብዙ ምክንያቶች መኖራቸውን በእርግጠኝነት አምናለሁ፡፡ አንደኛው ምክንያት፣ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ከሥልጣናቸው የተወገዱ መሆኑን ማረጋገጥ ነው፡፡ እሳቸው በሥልጣናቸው ላይ ያሉባት እያንዳንዷ ደቂቃና ሰዓት፣ ለምክር ቤቱ ብቻ ሳይሆን፣ ለአገሪቱም ትልቅ አደጋን የምታስከትል መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ “

ትራምፕን ከሥልጣን ለማስወገድ ያለቸው ቀን አጠያያቂ ሆናለች፡፡ ትራምፕ፣ ከሥልጣን የሚሰናበቱት፣ ተመራጩ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ ሥልጣናቸው በይፋ በሚረከቡበት፣ በሚቀጥለው ሳምንት ረቡእ፣ እኤአ ጥር 20/2021 ነው፡፡ አንዳንድ የሪፐብሊካን ምክር ቤት አባላት፣ ለባይደን በጻፉት ደብዳቤ እንዳስታወቁት፣ በዚህች አጭር ቀን ውስጥ፣ ፕሬዚዳንቱን ከሥልጣን የሚያባርር ውሳኔ ማሳለፍ አላስፈላጊና፣ ቁጣንም የሚቀሰቅስ ይላሉ፡፡

የኤለኖይ ተወካይ የሆኑት፣ ሪፐብሊካኑ የተወካዮች ምክር ቤት አባል፣ አደም ኪንዚንገር እንዲህ ይላሉ

“ፕሬዚዳንቱን ከሥልጣን ማባረር ትክክለኛ ውሳኔ አለመሆኑን በትክክል አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም አሁንም ተመልሶ እሳቸው የተበደሉ ያስመስላቸዋል፡፡ አሁን ጊዜው ዶናልድ ትራምፕ እጅግ በጣም፣ እጅግ በጣም መጥፎ ሆነው የሚታዩበት ወቅት ነው፡፡ ያንን መቸም በቃላት እንኳ መግለጽ አይቻልም አይደለም? ደጋፊዎቻቸውን ለአመጽ አነሳስተዋል፡፡ ይህ ቀን ሥራ አስፈጻሚው አካል ህግ አውጭውን አካል ያጠቃበት፣ በአሜሪካ ታሪክ በጣም መጥፎ ከሆኑ ቀናት አንዱ ነበር፡፡”

ፕሬዚዳንቱን ወይም ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ሥራቸውን በብቃት መምራት ባልቻሉ ጊዜ፣ እንዲነሱ የሚያደርገውን የህግ መንግስቱን 25ኛ ማሻሻያ የሚጥቀሱም ሰዎች አሉ፡፡

“በብቃት መምራት አለመቻል” ሲባል፣ በሞት በመለየት፣ ከሥልጣን በመባረር፣ በገዛ ፈቃድ በመልቀቅ፣ ሥራውን ለመስራት የሚያስችል የጉልበትም ሆነ የጤንነት አቅም ማጣት፣ የሚሉትን የሚያካትት ሊሆን ይችላል፡፡

እኤአ ታህሳስ 2019 ዓም፣ ህግ አውጭዎቹ የምክር ቤት አባላት፣ በፓርቲ ወገንተኝነት መስመር በተከፈሉበት ሁኔታ ውስጥ ሆነው በሰጡት ድምጽ፣ ፕሬዚዳንቱ ከሥልጣናቸው እንዲባረሩ የሚያስችለውን ውሳኔ ማሳለፋቸው ይታወሳል፡፡

በወቅቱ ትራምፕ የተከሰሱት፣ ሥልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀም፣ የዩክሬን ፕሬዚዳንት፣ ተቀናቃኛቸው የሆኑት ጆ ባይደን ላይ የሙስና ምርመራ እየተደረገ መሆኑን እንዲናገሩ ለማግባባት ሞክረዋል በሚል ነበር፡፡

ይሁን እንጂ፣ የእንደራሴዎቹ ምክር ቤት፣ የተወካዮቹን ምክር ቤት ውሳኔ ባለመቀበሉ ትራምፕ ከሥልጣናቸው ከመባረር ድነዋል፡፡

በአሜሪካ ታሪክ ከሥልጣኑ እንዲወገድ ሁለት ጊዜ ውሳኔ የተላለፈበት ፕሬዚዳንት የለም፡፡ ዘገባው በምክር ቤቱ የቪኦኤ ዘጋቢ የሚሼል ኲዪን ነው፡፡

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ፡፡

ህግ አውጭዎች ትራምፕን ከሥልጣን ስለማባረር እየተወያዩ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:42 0:00


XS
SM
MD
LG