“ግብረ ገብነት የጎደለው ተግባር በነባር ሕዝቦች ላይ ተፈጽሟል”
የቫቲካን ቤተ ክርስቲያን፣ በቅኝ ግዛት ወቅት የነበራት ተሳትፎ፣ “ሃይማኖታዊ አስተምህሮዋን የሚፃረር ነበር፤” በሚል ውግዝ አድርጋለች፡፡
አውሮፓውያን አፍሪቃን በቅኝ አገዛዝ በተቀራመቱበትና አሜሪካንን በያዙበት ወቅት፣ ቫቲካን፣ “ዐዲስ ስፍራዎችን ማሠሥ እና መውረስ አስተምህሮው ይፈቅዳል፤” በሚል ሰበብ፣ ለባሪያ ፍንገላ እና ለቅኝ አገዛዝ ምክንያታዊ ሽፋን ሰጥታ ነበር፡፡
ቅኝ ገዥዎች፣ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ ጳጳሳት ያኖሯቸውን ሰነዶች፣ ለባሪያ ፍንገላ እና ቅኝ ግዛት ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት ተጠቅመውበታል፤ ሲል የቫቲካን የባህል እና ሰብአዊ ልማት ክፍል፣ ዛሬ ኀሙስ ያወጣው መግለጫ አመልክቷል።
“የታሪክ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ግን፣ በወቅቱ በነበሩት ጳጳሳት የተጻፉት እና ከፖለቲካ ጥያቄ ጋራ የተያያዙት ሰነዶች፣ የካቶሊክ እምነት ነጸብራቅ አልነበሩም፤” ሲል የባህል እና ሰብአዊ ልማት ክፍሉ በመግለጫው በሃይማኖታዊ አስተምህሮው ቅቡልነት እንደሌለው አስረድቷል፡፡
“የታሪክ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ግን፣ በወቅቱ በነበሩት ጳጳሳት የተጻፉት እና ከፖለቲካ ጥያቄ ጋራ የተያያዙት ሰነዶች፣ የካቶሊክ እምነት ነጸብራቅ አልነበሩም፤”
“የቅኝ ግዛት ኃይሎች፣ ሰነዱን የፖለቲካቸው መጠቀሚያ በማድረግ፣ አንዳንዴም በሃይማኖታዊ መሪዎች ይኹንታ፣ ግብረ ገብነት የጎደለው ተግባር በነባር ሕዝቦች ላይ ፈጽመዋል፤” ሲል አክሏል መግለጫው፡፡
አፍሪካንና አሜሪካንን ለመያዝ፣ በስፔናውያንና በፖርቹጋሎች ጥቅም ላይ የዋሉትና በወቅቱ ጳጳሳት የተጻፉት ሰነዶች፣ “ነባር ሕዝቦች እንደሌሎች ሰዎች ኹሉ የተከበሩ ፍጡራን እንደኾኑ በበቂ አላሳየም፤” ብሏል መግለጫው።
“ስሕተት እንደነበር ለማሳወቅ እና ነባር ሕዝቦች ላይ ለተፈጸመው ሠቆቃ ይቅርታ መጠየቅ እንሻለን፤” ብላለች ቫቲካን፡፡
የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፣ “ክርስትናን ለማስፋፋት በሚል በምዕራባውያን ወራሪዎች ለተፈጸመው ሠቆቃ ተባባሪ ነበረች፤” የሚል ወቀሳ፣ ለረጅም ጊዜ ሲቀርብባት መቆይቱን የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል፡፡