በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዩክሬን ኃይሎች ሲቪዬሮዳኔትስክን ለቀው ሊወጡ ነው


ፎቶ ፋይል - የዩክሬን ታንክ ከባድ ውጊያ በሚካሄድበት በሲቪዬሮዳኔትስክ፣ ሉሃንስክ ክልል በግንባሩ ላይ እአአ ሰኔ 8/2022
ፎቶ ፋይል - የዩክሬን ታንክ ከባድ ውጊያ በሚካሄድበት በሲቪዬሮዳኔትስክ፣ ሉሃንስክ ክልል በግንባሩ ላይ እአአ ሰኔ 8/2022

የዩክሬን ኃይሎች ከተከበበቸው የሲቪዬሮዳኔትስክ ለቀው እንደሚወጡ በክልሉ የዩክሬን ወታደራዊ አዛዥ አስታወቁ፡፡“በሩሲያ ኃይሎች ያለማቋረጥ በወራት የምትደበደበውን ከተማ ይዞ መቆየቱ ትርጉም አይሰጥም” ብለዋል አዛዡ ጨምረው በሰጡት መግለጫ፡፡

በሌላም በኩል የአውሮፓ ፓርላማ በትናንት ሀሙስ ስብሰባው በጦርነት ውስጥ የምትገኘውን ዩክሬንን የአውሮፓ ህብረት አባል እጩነት እንድትሆን በሙሉ ድምጽ ተቀብሏል፡፡

ውሳኔው አራት ወራት የዘለቀውን የሩሲያን ወረራ በመመክት ላይ ለምትገኘው ዩክሬን፣ ግዙፍ የጦር መሳሪያዎችን በመደገፍ ላይ ወደሚገኘው የምዕራቡ ዓለም ለመቀላቀል የመጀመሪያው እምርጃ ነው ተብሏል፡፡

ፓርላማው የዩክሬንን እጩነት የተቀበለው 525 ለ45 በሆነ ልዩነትና በ14 የተአቅቦ ድምጽ መሆኑ ተዘግቧል፡፡

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ውሳኔውን አስመልክተው ባስተላለፉት የትዊት መልዕክት “ይህ ወቅት በዩክሬን አውሮፓ ግንኙነት ልዩና ታሪካዊ ነው... የዩክሬን የወደፊት ተስፋ በአውሮፓ ህብረት ውስጥ ነው” ብለዋል፡፡

በሌላኛው የማህበራዊ ሚዲያ መድረክ ኢንስታግራም ላይ ባስተላለፉት መልዕክትም “የእጩነትን ደረጃ አሁን አግኝተናል፡፡ ይህ ድላችን ነው” ብለዋል፡፡

ዩክሬክን የህብረቱ አባል ሆና የመታጨቱ ዜና የተሰማው ዩናይትድ ስቴትስ፣ ከአንድ ሳምንት በፊት ይፋ ካደረገችው የአንድ ቢሊዮን ዶላሩ ድጋፍ ሌላ፣ አንዳንድ ተጨማሪ የመካከለኛ ርቀት ሮኬቶችን ጨምሮ፣ የ450ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ወታደራዊ ድጋፍ ለዩክሬን እየላከች መሆኑን ባስታወቀችበት ወቅት ነው፡፡

የዩክሬን ፓርላማ ሊቀመንበር ሩስላን ስቴፋንቸክ በፌስ ቡክ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት “ዩክሬን የአውሮፓ ህብረት አባል አገር ነች፣ ለዚህ መብት ደግሞ በጦር ሜዳ ብቻ ሳይሆን በህጉም መድረክ እንፋለማን” በማለት የአውሮፓ ህብረት ህግ አውጭዎች ስለሰጡት ድጋፍ አመስግነዋል፡፡

ለአውሮፓ ህብረት የታጩ እነዚህ አገራት 27 አባላት ወዳሉት ህብረት ለመቀላቀል ጠንክራ የሆኑ የፖለቲካና የማህበራዊ ለውጦችን ማሳየት ይኖርባቸዋል፡፡

የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዚዳን ኡርሱላ ቫን ደር ሌይን “ዩክሬን ከወዲሁ 70 ከመቶ የሚሆኑትን የአውሮፓ ህብረት ህግጋት፣ ሥርዐቶችና መስፈርቶችን አሟልታለች” ያሉ ሲሆን “ይሁን እንጂ የህግ የበላይነት፣ የአገዛዙን ከበርቴዎችና ጸረ ሙስናን እንዲሁም መሠራታዊ መብቶችን በሚመለከት ብዙ መሠራት ይኖርበታል” ብለዋል፡፡

የ27ቱንም የአውሮፓ ህብረት መንግሥታት መሪዎችን የሚያካትተው የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት በዩክሬን አባልነት ላይ የመጨረሻውን ድምጽ ይሰጣል፡፡ የሚሰጠው ድምጽ ሙሉ ሙሉ መሆን ይኖርበታል፡፡ ዲፕሎማቶች እንደሚሉት ሂደቱ አስርት ዓመታትን ሊፈጅ ይችላል፡፡

“ዩክሬናውያን የአውሮፓውያን ቤተሰብ ናቸው፡፡ የዩክሬናውያን የወደፊት ተስፋ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ነው” ያሉት የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል “ዛሬ አብረን የምንጓዘው ረጅሙ ጉዞ የተጀመረበት እለት ነው” ብለዋል፡፡

በብራስልስ የተሰበሰቡት የአውሮፓ ህብረት መሪዎች በዩክሬን ያለው ጦርነት፣ በዓለም የምግብ ደህንነት ላይ በሚያሳድረው ተጽእኖና፣ እንዲሁም በአውሮፓ ተጨማሪ የኢኮኖሚ፣ ወታደራዊና ሰብአዊ ድጋፍ ላይ መነጋገራቸው ተመልክቷል፡፡

በሌላም በኩል የዩክሬን ፕሬዚዳንት ዜለንስኪ ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን ዶናባስ ግዛት ከባድ የአየርና የመድፍ ድብደባዎችን ያካሄደች መሆኑን ገልጸው፣ ዓላማው “ቀስ በቀስ ጠቅላላውን ዶናባስ ለማውደም” ነው ብለዋል፡፡

የሩሲያውን ጥቃት ለመቋቋም የሳቸው ኃይሎች ተመጣጣኝ የጦር መሳሪያዎችን በአፋጣኝ እንዲያገኙም የዩክሬኑ መሪ ተናግረዋል፡፡

XS
SM
MD
LG