በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዩክሬኑ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ ሀገራት ገለልተኛነት “በጣም አበሳጭቶናል” አሉ


የዩክሬኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሜትሮ ኩሌባ
የዩክሬኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሜትሮ ኩሌባ

የዩክሬኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሜትሮ ኩሌባ፣ ሩሲያ በአገራቸው የምታካሒደውን ጦርነት በተመለከተ፣ የአፍሪካ ሀገራት እያሳዩ ያሉትን ገለልተኛ አቋም እንዲቀይሩ ጠይቀዋል።

ትላንት በኢትዮጵያ ዋና መዲና ዐዲስ አበባ፣ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የዩክሬኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር “አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ዝምታን መምረጣቸው በጣም አበሳጭቶናል፤” ብለዋል።

ሩሲያ፣ የዩክሬንን ሉዓላዊነት በጣሰችበት ኹኔታ፣ የአፍሪካ ሀገራት፥ ለዩክሬን ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ፣ ኩሌባ ጥሪ አድርገዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ፣ የሩሲያን ወረራ ለማውገዝ ድምፅ በሚሰጥበት ወቅት፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ድምፀ ተአቅቦ አድርገዋል።

ሩሲያ፣ በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት እግር ተክላ ስትገኝ፣ ዋግነር በመባል የሚታወቀው የግል ቅጥር ወታደራዊ ኃይል፣ በተለይ በምዕራብ አፍሪካ ይንቀሳቀሳል። ሩሲያ እና ደቡብ አፍሪካ፣ በቅርቡ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ አድርገዋል። ሩሲያ በመጪው ሐምሌ፣ የ“አፍሪካ ሩሲያ ጉባኤ” የማካሔድ ዕቅድ አላት፡፡

ኩሌባ በተጨማሪም፣ የአፍሪካ ሀገራት፣ ባለፈው ታኅሣሥ ወር፣ በዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ የቀረበውን ባለ ዐሥር ነጥብ የሰላም ዕቅድ እንዲደግፉ ጥሪ አድርገዋል። በኃይል፣ በቴክኖሎጂ እና በፋርማሲ ምርት ዘርፎች፣ ዩክሬን ከአፍሪካ አህጉር ጋራ የተሻለ ትብብር ማድረግ እንደምትሻም ተናግረዋል።

ኩሌባ፣ በዚኹ የአፍሪካ ጉብኝታቸው፣ ወደ ሞሮኮ እና ሩዋንዳም እንደሚያቀኑ ለማወቅ ተችሏል።

በዐዲስ አበባ ቆይታቸው፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንዲሁም ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት እና ከወቅቱ የኅብረቱ ፕሬዚዳንት የኮሞሮስ ፕሬዚዳንት አዛሊ አሱማኒ ጋራ ተወያይተዋል።

XS
SM
MD
LG