በሞስኮ፣ በአደገኛ ዕፅ ዝውውር ተይዞ የተከሠሠው፣ የዩናይትድ ስቴትስ ሙዚቀኛ እና የቀድሞ አየር ወለድ አባል የነበረ አሜሪካዊ፣ ፍርድ ቤት መቅረቡን፣ ሮይተርስ ዘገበ፡፡
በመንግሥት ቴሌቪዥን እንደታየው፣ አሜሪካዊው ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት፣ የብረት እጥር በኾነ የተከሣሽ መቆሚያ ውስጥ እንዳለ መታየቱ ተዘግቧል፡፡
የሩሲያ ፍርድ ቤት፣ የ51 ዓመቱ አሜሪካዊ ማይክል ትራቪስ ሊክ፣ በማለት የገለጸው ተከሣሹ፣ ቀደም ሲል በሩሲያ “ሎቪ ኖች” ተብሎ በሚጠራው የሮክ ባንድ፣ ሙዚቀኛ እና የዜማ ደራሲ እንደነበር ተወስቷል፡፡
“ሩሲያ 24” የተባለው ቴሌቪዥን፣ ባለፈው ቅዳሜ፣ የተከሣሹን ምስል ያሳየው፣ ተከሣሹ፥ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ከተያዘ በኋላ እንደኾነ ተነግሯል፡፡
ወጣቶችን ባሳተፈ የአደገኛ ዕፅ ዝውውር እና ንግድ የተከሠሠው ሊክ፣ እ.አ.አ እስከ ነሐሴ 6 ቀን 2023 ድረስ በእስር እንደሚቆይ፣ የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል፡፡
ሊክ፣ ጠበቃ ያለው ስለመኾኑ ግልጽ አይደለም፤ ያለው የሮይተርስ ዘገባ፣ በሩሲያውያን ቁጥጥር ሥር ያለውን የተከሣሹን አስተያየት ለማግኘት አለመቻሉን አስታውቋል፡፡
ዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ፣ “በቅርቡ ሞስኮ ውስጥ፣ አንድ አሜሪካዊ በቁጥጥር ሥር ስለ መዋሉ የወጡትን ዘገባዎች እናውቃለን፤” ብለዋል፡፡
ቃል አቀባዩ አክለውም፣ ሚኒስቴሩ፥ አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ዜጋ፣ በውጭ አገር በታሰረ ጊዜ፣ ወዲያኑ፣ የዚያን አገር ቆንስል አግኝቶበማነጋገር፣ የሚያስፈልገውን ርዳታ ሁሉ ያገኝ ዘንድ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
ይኹን እንጂ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት፣ የቆንስሉ ርዳታ፣ እስከ አሁን ለተከሣሹ ሊክ መስጠት ስለመቻላቸው፣ ቃል አቀባዩ የገለጹት ነገር የለም፡፡
የዩክሬኑ ጦርነት ከተጀመረ ካለፈው ዓመት የካቲት አንሥቶ፣ ሩሲያ ውስጥ ሊደርስባቸውን የሚችለውን የዘፈቀደ እስር እና እንግልት ለማስወገድ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ዜጎች፥ ሩሲያን ለቀው እንዲወጡ በተደጋጋሚ ስታሳስብ መቆየቷ ተመልክቷል፡፡