በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፑቲን: ሩሲያ የዩክሬን እህል እንዲጫን ከገባችበት ስምምነት ለመውጣት እያሰበችበት ነው


የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን
የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን

ሩሲያ፣ የዩክሬን እህል ከጥቁር ባሕር ወደብ ወደ ዓለም ገበያ እንዲጫን ከተደረሰው ስምምነት ለመውጣት እያሰበች እንደሆነ፣ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ትላንት ማክሰኞ አስታወቁ፡፡

ፑቲን፣ የሩሲያን ከስምምነቱ የመውጣት ምክንያት ሲያስረዱም፣ “ምዕራቡ ዓለም፥ የሩሲያን ሸቀጦች ለሰፊው የዓለም ክፍል ለማዳረስ ከገባው ቃል አንዱንም ባለማክበር በሞስኮ ላይ ማጭበርበር ፈጽሟል፤” ብለዋል፡፡

ዩክሬን፣ ምርቶቿን ለዓለም ገበያ እንድታቀርብ የሚፈቅደው ስምምነት የተደረሰው፣ ባለፈው ዓመት ሐምሌ፣ በተባበሩት መንግሥታት እና በቱርክ አደራዳሪነት እንደነበረ ተመልክቷል፡፡

ዓለም አቀፉ የምግብ ቀውስ፣ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ትልቁ በኾነው “የአውሮፓ ሰው ጨራሽ ግጭት” ሳቢያ እየተባባሰ መምጣቱን፣ የተባበሩት መንግሥታት አመልክቷል፡፡

ሞስኮ፣ ስምምነቱን እንድትቀበል ለማግባባት የተደረሰበት የሦስት ዓመት ውል፣ ሩሲያም የራሷን ምግብ እና ማዳበሪያዎች ለዓለም ገበያ ለማቅረብ እንድትችል በመርዳት፣ የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣናት ከገቡት ቃል ጋራ የተሳሰረ እንደኾነ ተገልጿል፡፡

ይኹን እንጂ ፑቲን፣ ጉዳዩን ከምዕራባውያኑ ያለመታመን ጋራ በማያያዝ፣ “አሁን፣ ከዚኽ የእህል ስምምነት ለመውጣት እያሰብንበት ነው፤” ሲሉ፣ ለሩሲያ የጦርነት እና ወታደራዊ ዘጋቢዎች ተናግረዋል፡፡

ፑቲን አክለውም፣ “እንዳለመታደል ኾኖ፣ አሁንም በድጋሚ ተጭበርብረናል፡፡ የእህል አቅርቦቱን ለውጭ ገበያዎች ነፃ ለማድረግ፣ ምዕራባውያን በተባበሩት መንግሥት አመራር ሊያሟሏቸው የሚገቧቸው ብዙ ነገሮች ነበሩ፤ አንዳቸውም አልተፈጸሙም፤” ብለዋል፡፡

ምዕራባውያን፣ ሩሲያ እ.አ.አ. የካቲት 24 ቀን፣ በዩክሬን ላይ “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” ስትል የጠራችውን ወረራ ከፈጸመች ወዲህ፣ እስከ ዛሬ ደርሶባት የማያውቀውን ጠንካራ ማዕቀብ ጥለውባታል፡፡

XS
SM
MD
LG